(የግል ምልከታ)
ንቡር ጠቃሽነት በታሪክ፣ በማህበረሰብ የጋራ አኗኗር፣ ሐይማኖታዊና ልማዳዊ ክስተቶች ውስጥ የታለፉ ኩነቶችን በስነ-ጽሑፍ ሲጠቀስ፣ በሙዚቃ ሲዳሰስ የምናውቀው ነው።
በሙዚቃ ስል ምን ማለቴ እንደሆነ ግልጽ ለማድረግ ያህል እነዚህን እንደምሳሌ ልጥቀስ…
~የጂጂ “ናፈቀኝ” ውስጥ ያሉትን እንደ “አያ ታዴ ሆዴ” ያሉ እውነተኛ ባለታሪኮችን፤
~የግዛቸው ተ/ማርያም “ሊጋባው በየነ” ጠጅ ጠጣ ሲሉት ውሃ የሚለምነውን ኩሩ፤
እና
~የየማ ዘፈን ውስጥ የተጠቀሰውን የአራዳውን ሞጭላፊ “ሌቦ ሳህሌ” በሙዚቃ የተወሱ የታሪክ “ንቡር ጠቃሽ” ምሳሌ መሆን ከሚችሉ ውስጥ ጥቂቶች ናቸው።
ነገር ግን ንቡር ጠቃሽነት ለሳቅና ለልግጫ ተብሎ ከተነገረ ጨዋታ ውስጥ ሲፈለቀቅ ግን ይኸው ገና አሁን “ባለቤቴ” በተሰኘ ስራ ውስጥ አደመጥኩኝ።
በዚህ ዘፈን ውስጥ ንቡር ተጠቃሽ የሆነው ተምሳሌታዊ መነሻ ሀሳብ በአንድ ወቅት የሳቅንበት፣ ለልግጫና ለተረብ ያመቻቸነው ቀልድ መሳይ ኩነት መሆኑን ድንቅ ነው።
አንድ ጥላ ይዞ በዝናብ አትክልት ውሃ የሚያጠጣ “Jiል ነው” ስንል ፈርደን፤ እግር አንስተን በድድ ሳይቀር ያስካካንበትን ሰው አስታወሳችሁት? እስኪ አሁን ከዛ ሰውና ከቀልዱ ምን ቁምነገር ይወጣዋል ተብሎ ይታሰባል?
ይሄንን ግን ናትናኤል ግርማቸው በ”ባለቤቴ” ዘፈን ውስጥ አድርጎ አስደነቀኝ!
እዚህ ዘፈን ውስጥ የገጣሚ ሦስተኛ ዐይን በጉልህ ይታያል…ገጣሚ ቃላት ሰካክቶ፣ ቤት መቶና ቤት ደፍቶ ገጠምኩኝ የሚል ብቻ ሳይሆን ፈላስፋም ጭምር እንደሆነ ምስክር የሆነ ግጥም ነው የ”ባለቤቴ” ዘፈን ግጥም ።
(“ግጥም ያልተዝረከዘረከ ፍልስፍና ነው” አንዲል ገጣሚው)
ያውም ፍልስፍናን ለመሸከም ጉልበቱ ይብረከረካል፣ ጫንቃው አይችልም ተብሎ በሚታማ በዘፈን ግጥም ነው ይሄ የሆነው። እኛ ተራ ተርታዎቹ አይተን የሳቅንበትን፣ መዘባበቻ ያደረግነውን፣ ለተረብ ያቀባበልነውን ምስላዊ ክስተት በገጣሚ ልቦናው መዝኖ “እውነቱ ወዲህ ነው” አለን ገጣሚው ናትናኤል ግርማቸው።
በዛ “Jiል” ስንል ተረብ በወረወርንበት ላይ አብሮን ሳያብር የተወረወረውን የተረብ ድንጋይ ሰብስቦ ግሩም የሆነ የግጥም ኪነ-ህንጻ ገንብቶበት ይኸው አለን።
በ “ባለቤቴ” የዘፈን ግጥም ናትናኤል ግርማቸው እኚህን ሀሳቦች ያነሳሳል…
ከዶፍና ዝናብ ሽሽት ከቤታቸው ከተጠለሉት እንደ አንዳቸው ሳይሆን “ዝናብን ሳይፈራ”፣ “ሙቀት ሳያምረው” ለአበቦቹ የዕለት ውሃቸውን የሚቸር ሰው፤ ከማስደመጥ ባለፈ በገለጻ ምስል ተከስቶልን “ቆሞ” ስናይ ዘፈኑ ይጀምራል።
ለደመናው ሳይታይ ለዶፍ ለክረምቱ
ሁሉም ተጠልሎ ሳለ በየቤቱ
ዝናቡን ሳይፈራ ሳያምረው ሙቀቱ
ከአበቦቹ መሐል ቆሟል አንድ ብርቱ።
እኛ በዶፍ ዝናብ አትክልት በማጠጣቱ አላዋቂነት ስናላግጥና ስንስቅ፤ ነገር ግን ያ ሰው ንፉግነትን የሚጸየፍ “ቸር ሰው” መሆኑን በገጸ-ሰቧ በኩል፣ በቤተልሔም ድምጽ ስህተታችን ተነግሮን አላዋቂነታችን ይታረማል።
በዝናብ አካሉም በዶፉ እየረሰረሰ
የአትክልቶቹን ሥር ሲያጠጣ
የልምዱን ውሃ እያፈሰሰ
አሉት የማነው Jiል ያን አትክልተኛ
ሳቁበት እንደሞኝ ወይኔ…
አላወቁ እነሱ ዝናብ መጣ ቀረ
ንፍገትን ለልቡ እንዳላስተማረ…
በዘፈኑ ውስጥ የተገለጸው ሰው እኛ በምስል እንደምናውቀው ጥላ በመያዝ ዝናብ የሚሸሽ አይደለም። ከሚያጠጣው ውሃ ውጪ በእጁ አንዳችም መጠለያ ሳይዝ የቆመና ለአትክልቶቹ እንዳልነፈገው ውሃ ለራሱም የዝናብ እርጥበት የሚቀበል ነው። ለራሱ ጥላ ከመሻት ይልቅ ሌሎች ጥላ የሆነ ምስጉን እና ትሁት ሰው ነው።
(በኋላ ላይ ገጸ-ሰቧ የእሱን አይነት ለኑሮዋ ስትሻ “ሁነኝ ጥላ” ስትል የምንሰማት ለዚህ ይሆናል። )
ለአትክልልቶቹ ሲል ከዝናብ ሳይጠለልና “ዝናብ አለ” ሳይል የዕለት ሀቃቸውን ያለ ንፍገት ውሃ የሚያጠጣ ባለ “አጸድ” እንዲህ ያለ የፍቅር ጥጉ ሰው ላይ ቢገለጥ፣ ለፍቅሩና ለሚስቱ ቢሆን እንዴት ያለ እንደሚሆን ደግሞ በዘፈኑ ይጠየቃል።
ይህ ነው ካልቀረ ለእኔ የፍቅር ጥግ
ዝናብ አለ ብሎ ውሃ አለመንፈግ
አሰብኩት ከሆነ እንዲህ ለአትክልቱ
እንዴት መልካም ይሆን ለሚወዳት ሚስቱ?
ባለቤቱ ባለቤቱ
ናት ዕድላም ባለቤቱ
ሚስቱ!
እንዲህ ያለን ወንድ ወይም እንዲል ያለን ወንድ የመሰለ አንዲት ሴት ለሕይወት አጋር አድርጋ ብትሻው ስህተት ይሆናል? አይሆንም አይደል? ለዛም ነው ከላይ የተገለጸውን “ባለ አጸድ ሰው” የመሰለ እኔም ቢገጥመኝ ብላ ምኞቷን የምታስደምጠን።
ልክ እንደ አትክልተኛው:- “ሆነ አልሆነ” ዘነበ አልዘነበ፣ ሞላ ጎደለ፣ ታጣ ተገኘ ሳይል ፍቅርና መውደዱን ያለስስት የሚሰጥ፤ በአበባ አይነትና ልክ ፍቅርን መንከባከብ የሚችል የፍቅር አትክልተኛ፣ የፍቅር “ባለ አጸድ” ወንድ ባገኝ ስትል ትመኛለች።
ያስባል…ልቤም ስለራሱ
የነገውን መንገድ
ባለም ውጣ ውረድ
ሆነ አልሆነ ብሎ የማይሰስት መውደድ።
ፍቅሩን እንዳበባ ሁሌ የሚንከባከብ
ባገኝ የራሴን ሰው የእኔን…
ልክ እንደ ባለ አጸዱ- በሁኔታዎች የማይታሰር፣ ለአጋጣሚ እጅ የማይሰጥ ፣ የራሱን ሀላፊነትና ድርሻ ጠንቅቆ የተረዳ፣ የሚጠበቅበትን የሚያውቅ፣ “ለመውደዱ ጽኑ” የሆነ ሰው ትሻለች።
ቢዘንብም ቢያካፋ
ከጎኔ የማይጠፋ
እንደ ባለ አጸዱ
ጽኑ ለመውደዱ
እንዲህ ያለው ወንድ አንዲትን ሴት ፍቅር በማጣት ከሚመጣ መክሰም ይታደጋል ብላ ታምናለች የ”ባለቤቴ” ዘፈን ገጸ-ሰብ። እንዲህ ያለውን ሰው “ባለቤቷ”፣ የሕይወት አጋሯ አድርጋ፤ የምታጋራውን የጋራ ኩነትንና እውነትን አጥብቃ ትመኛለች። እንዲህ ካለው አጋር ደግሞ ልክ እንደሱ ያለ ንፍገትን የማያውቅ፤ ቸር እና ቅን ሰው ወልዳለት ማቀፍ ትልቁ ግቧ ሆኖ “ነጻነቷን ሰጥታ፣ ልጅነቷን የተወች” እናት ለመሆን እየተመኘች ዘፈኑ ያበቃል።
ሳላውቅህ ልንገርህ የነገ ውሃ አጣጬ
አርገኝ እንዳልከስም ፍቅርን ተጠምቼ
ብቻዬን አልሙቃት የነገዋን ጸሐይ
ሦስት አርገን አንድ ሆነህ ልቀፍ አንተን መሳይ
እሰረኝ በፍቅር ውሰድ ነፃነቴን
እናት አርገኝና ልተው ልጅነቴን።
ባለቤቴ ባለቤቴ ባለቤቴ
ባለቤቴ “ሁነኝ ጥላ” ባለቤቴ።
በአጠቃላይ “ባለቤቴ” ዘፈን ቢፈለቀቅ ብዙ ሀሳብ ብዙ እውነት ብዙ መገረም የሚወጣው የ”ደስተኛ” አልበም አንዱ መዋጮ ሲሆን፤ ይህ ዘፈን ይበልጥ “ከልግጫ ውስጥ የተገኘ ግሩም እውነት” ስለመሆኑ ለመፍረድ ጆሮ እና ልቦና ሰጥተን እናድምጥ እላለሁ።
Source: GetuTemesgen








No comments yet.