የጣና ቅዱስ ቂርቆስ ገዳም የ3.3 ቢሊዮን ብር የሆስፒታል ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ

- Advertisement -
Sidebar AD

የባሕር ዳር እና ሰሜን ጎጃም አኅጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃምን ጨምሮ በብፁዓን አባቶች አባራኪነት፣ የርእሰ አድባራት ወገዳማት ጣና ቅዱስ ቂርቆስ አንድነት ገዳም የ፬ቱ ጉባኤያት የምስክር ጉባኤ ቤት የሚያስገነባው “ሰንፔር ጠቅላላ ሆስፒታል” የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ።

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የፕሮጀክቱ ይፋዊ ማስጀመሪያ ተከናውኗል።
የጉባኤ ቤቱ መምህር ርእሰ ሊቃውንት አባ ገብረ ኪዳን ግርማ ስለ ፕሮጀክቱ ዓላማ በሰጡት ማብራሪያ፤ ሆስፒታሉ ተስፋ ለቆረጡና በሱስ ለተጎዱ ወገኖች ማገገሚያን ጨምሮ የአእምሮ፣ የእናቶችና ሕጻናት፣ የልብ፣ የኩላሊት እና የካንሰር ሕክምና ማዕከላትን ያካተተ ሰፊ የሕክምና መንደር እንደሚኖረው ገልጸዋል።

ግንባታው ቤተ ክርስቲያን ለሀገር ያበረከተችውን ታሪካዊ አስተዋጽኦ በሕክምናው ዘርፍ ለማስቀጠልና ሀገር በቀል የሕክምና ጥበብን ለማስፋፋት ያለመ መሆኑን የጠቀሱት ርእሰ ሊቃውንት፣ አበው ሊቃነ ጳጳሳትና መነኮሳትም ክብራቸውን ጠብቀው የሚታከሙበት እንደሚሆን
አስታውቀዋል

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው በበኩላቸው ሃይማኖት ሳይለይ ሕዝብን በቅንነት ለማገልገል የሚሠሩ አባቶችን ማገዝ ሕዝብንና ሀገርን ማገልገል በመሆኑ ፕሮጀክቱ መንግሥትና ሃይማኖት ለሕዝብ ጥቅም በጋራ እንደሚሠሩ ማሳያ ነው ብለዋል።
በ9 ዓመታት ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት ይበቃል ተብሎ የታቀደው ይህ ግዙፍ የጠቅላላ ሆስፒታል ፕሮጀክት እስከ 3.3 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደሚጠይቅ ተገልጿል።






Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1