በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በምስራቅ በለሳ የሚገኘው የሙት አንሳ ማር ቅዱስ ሚካኤል አንድነት ገዳም የመሰረተ ልማት እና የአካባቢ ጥበቃ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ተጎበኘ።
ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት በ2015 ዓ.ም. በመስክ ጥናትና በህጋዊነት ማረጋገጫ ተጀምሮ፣ ጥር 2016 ዓ.ም. መሰረት ድንጋይ ከተጣለ በኋላ በ133 የሥራ ቀናት ውስጥ የመጀመሪያው ምዕራፍ ጥር 2017 ዓ.ም ተጠናቋል።
📍የመጀመሪያው ምዕራፍ አበይት ስኬቶች፦
📌 የመነኮሳት በዓታት
4 መነኮሳትን በጋራ ማስተናገድ የሚችሉ 19 ክፍሎች (እያንዳንዱ 12 ካሬ ሜትር) ተገንብተዋል። ክፍሎቹ ሙሉ መንፈሳዊ መጻሕፍት (መጽሐፍ ቅዱስ፣ ድርሳነ ሚካኤል፣ አርጋኖን) የተሟሉላቸው ናቸው።
📌 የአካባቢ ጥበቃና ልማት
የመሬት መንሸራተትን ለመከላከል ከ2 ሜትር በላይ ጥልቀት ያላቸው የጋቢዮን ግንባታዎች የተሰሩ ሲሆን፣ ከባህር ዳር እና ከሌሎች አካባቢዎች የተጓጓዙ የዛፍ ችግኞች በግቢው ውስጥ ተተክለዋል።
📌 የእጅ ስራ ማዕከል (ሸማ ቤት)
መነኮሳቱ የራሳቸውን አልባሳትና የገዳሙን ፍላጎት በራሳቸው አቅም እንዲሸፍኑ የሚያስችል የሸማ መስሪያ ማዕከልና መጋዘን ተገንብቷል። የተመረቱ ምርቶች ለገበያ እየቀረቡ ይገኛሉ።
📌የመንገድና መሰረተ ልማት
6 ሜትር ስፋት ያለው 8 ኪሎ ሜትር የጥርጊያ መንገድ፣ 170 ሜትር የድንጋይ ንጣፍ መንገድ እና ወደ ጸበል ቦታ የሚወስድ የድንጋይ ንጣፍ ደረጃ ተሰርቷል።
📌 በሶላር መብራት ተገጥሞ በግቢው ውስጥ እና በክፍሎች ውስጥ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
📌ቁሳቁስና እንስሳት
ለአገልግሎትና ለጭነት የሚሆኑ በቅሎዎች፣ አህዮች፣ ከብቶች፣ በጎችና ፍየሎች ተገዝተዋል።
ያጋጠሙ ፈተናዎች፦
የፀጥታ ስጋት፣ የመሰረተ ልማት አለመኖር እና የመንገድ መዘጋት ዋና ዋና ማነቆዎች ነበሩ። ቡድኑ ቁሳቁስ ለማጓጓዝ ከመካከለኛው ጎንደር ተነስቶ በደቡብ ጎንደር በኩል ረጅም መንገድ ለመዞር ተገዷል። በተጨማሪም በወር እስከ 15 ቀናት አካባቢ በሃይማኖታዊ ስርዓት ምክንያት ስራ የሚቆም ቢሆንም፣ ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት ጊዜ ተጠናቋል።
🏗️ የሁለተኛው ምዕራፍ እንቅስቃሴ (ከህዳር 2018 ዓ.ም. ጀምሮ)፦
📌 በ1,300 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው የቤተክርስቲያኑ የፋውንዴሽን እና የአፈር ሙላት ስራ ተጠናቆ ለጣራና ለግድግዳ ስራ ዝግጁ ሆኗል።
📌 5 ክፍሎች ያሉት የጳጳሳትና የእንግዶች ማረፊያ ህንጻ ግንባታ እየተጠናቀቀ ይገኛል።
📌 የቤተክርስቲያኑ ግንባታ ብቻ እስከ 30 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚጠይቅ ሲሆን፣ ሙሉ ፕሮጀክቱ ከተያዘለት 3 ዓመት ከ6 ወር ቀድሞ በ2 ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
📌 የመነኮሳት መኖሪያ
በተከናወነው የህንፃ ግንባታ መርሃ-ግብር ለእናቶች (መነኮሳት) ቅድሚያ ተሰጥቶ አጠቃላይ የማረፊያ ክፍሎች ግንባታ ተጠናቋል።
በሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ የአባት መነኮሳት መኖሪያ እያንዳንዱ ክፍል 12 ካሬ ሜትር ስፋት ያለውና እስከ 4 መነኮሳትን ማስተናገድ በሚያስችል መልኩ የተቃኘ ነው። በተጨማሪም 18 ካሬ ሜትር ስፋት ያላቸው ክፍሎች ከተለያዩ ገዳማት ለልምድ ልውውጥና ለመንፈሳዊ አገልግሎት ለሚመጡ እንግዳ መነኮሳት ማረፊያነት የተዘጋጁ ናቸው። በአጠቃላይ መኖሪያው እስከ 64 አባቶችን የመያዝ አቅም አለው። በሚቀጥሉት 1 ወር ባለው ጊዜ የማጠናቀቂያ ስራዎች ተሰርተው ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ገዳሙ በሰው እጅ ሳይጠበቅ በራሱ የኢኮኖሚ አቅም መቆም የሚያስችለውን መሰረት ለመጣል ባለው የማምረቻ ሼድ ውስጥ ዘመናዊ የእንጨት፣ የብረትና የጥገና ስራዎች ተጀምረዋል። በዚህ ማምረቻ ውስጥ መነኮሳቱና ሰራተኞቹ በራሳቸው አቅም የደጃፍ በሮችን፣ የብረት ስራዎችን እንዲሁም የፎጣና የሽመና ምርቶችን ማምረትና መጠገን የሚያስችላቸው ስልጠናና የስራ አካባቢ ተመቻችቶላቸዋል። ይህም ገዳሙ በምግብና በቁሳቁስ ራሱን እንዲችል ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል።
የማዕድ ቤትና የሊቃውንት ማደሪያ
አጋፔ ማዕድ፦ መነኮሳቱና የመስክ ሰራተኞቹ በአንድነት ተሰብስበው ጸሎት ካደረጉ በኋላ በማህበር ማዕድ የሚቀምሱበት ሰፊ አዳራሽ ተገንብቶ ዝግጁ ሆኗል።
የሊቃውንት ማደሪያ፦ 9 ዘመናዊ ክፍሎችን ያካተተ ህንፃ የተገነባ ሲሆን፣ ካህናት፣ ዲያቆናትና አርድእት በተለየ ሁኔታ የሚያርፉበት ነው። የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ፣ የመጸዳጃና የሻወር ቤቶች ግንባታ እየተሰራ ይገኛል።
የቀጣይ ምዕራፍና የጸበል ቦታዎች ዕቅድ
ለጸበልተኞች፣ ለሱባዔተኞች፣ ለነፍሰ ጡሮች፣ ለሕፃናት እና ልዩ ትኩረት ለሚሹ (እንደ የስኳርና የኤች.አይ.ቪ መድኃኒት ለሚወስዱ) ታካሚዎች ምቹ የሆኑ የጸበልና የመጠለያ ቦታዎች፣ የሎከር እና የምግብ አቅርቦት አገልግሎቶች በዲዛይን ተካተዋል።
⚠️ የዋጋ ንረትና የትራንስፖርት ተጽዕኖ፦
የገበያ ዋጋ እና የትራንስፖርት ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። ቀደም ሲል በአንድ የጭነት መኪና እስከ 38 ሺህ ብር የነበረው የጠጠር ማጓጓዣ ወጪ አሁን እስከ 100 ሺህ እና 110 ሺህ ብር ደርሷል። በተጨማሪም ቁሳቁስ ከአዲስ አበባ እና ከሌሎች አካባቢዎች ለማድረስ የነዳጅ እጥረትና የመንገድ ጥገና ታክሎበት ከ2 እስከ 5 ቀናት ይወስዳል ይህም የትራንስፖርት ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አድርጎታል።
በቀጣይ ክፍል የሙት አንሳ ማር ቅዱስ ሚካኤል አንድነት ገዳም በዙ ሀሙሲት ከተማ እየተሰሩ የልማት ስራዎች ይዘን እንቀርባለን።
ይቀጥላል…
ፎቶ ከበደ መክብብ



Source: FastMereja









No comments yet.