” ቢዘንብም ቢያካፋም ከጎኔ የማይጠፋ

- Advertisement -
Sidebar AD

እንደ ባለ አጸዱ ጽኑ ለመውደዱ
ሳላውቅህ ልንገርህ የነገ ውሀ አጣጬ
አርገኝ እንዳልከስም ፍቅርን ተጠምቼ ”

እያለች ምኞቷን ፣ መሻቷን ፣ የወደፊት ህልሟን ትነግረናለች ። መልካምነት መስጠት ብቻ ሳይሆን መቀበልንም ይፈልጋል ። ምርጥ ዘር ምርጥ አፈርንም ይፈልጋል ። በተዘራበት ሁሉ አይበቅልም ። እንደ እሷ የሚረዳ ካልተገኘ ሌሎቹ እንዳሉት ” የማነው ሞኝ ? ” ያስብላል ።

በርዕሰ ጉዳይ ደረጃ የዚህ የወደድኩት ብርቱ አትክልተኛ ተቃራኒ ቢሆንም የእኔ ከ1ኛ – 3ኛ ” ቻው ( ዎ ) ” ነው ።

” አልነበረም ከዓይን የተሰወረ
መንገድህን ሳላየው መች ቀረ
ሰነባብቷል መንፈስህ ሸፍቷል
ልቤን ልብህ ቻው ካለው ቆይቷል ።
አልታወጀም እንጂ ፊትም የእኛ ነገር
የተለያየነው አብረን ሆነን ነበር ።
እንባዬ ተማጽኖህ እንዳያስታርቀን
ያለቀው ያኔ ነው ልብህ የሄደ ቀን ።
እያንዳንዱን ቀናት በእንባ እየሰፈርኩኝ
ቻው ስልህ ኖሬያለሁ እየሸራረፍኩኝ ።
ዛሬም ለበደልህ አረከኝ ጣል ጣል
ቻው ማለት ብቻ ነው የቀረኝ አንድ ቃል ። ”

ይኽ መቸም በየፍቅር ጎጆው ፣ በየትዳር ማጀቱ ፣ በየጓደኝነቱና ወዳጅነቱ አደባባይ የሚታይ የወቅቱ እውነታ ነው ። በየግንኙነታችን ” ቻው ማለት ብቻ ነው የቀረኝ አንድ ቃል ” ። አብዛኛዎቻችን አንድ ላይ ቆመናል እንጂ አብረን አይደለንም ። ” አንድ ላይ ብንሆንም ተለያይተናል ” እንዳለው ድምጻዊው ። እግሮቻችን ብቻ አብረው ይጓዛሉ ፤ አካላችን አንድ ላይ ይታያል ፤ ነፍስ የሌለው ስጋ ነው ። አብረን ውለን እናድራለን ፤ በልባችን ግን ተለያይተናል ። አልታወቀን ይሆናል እንጂ እንደ ግልም ፣ እንደ ሀገርም እንዲህ ሆነናል ። ለዚህ ነው አሁን ያለንበት ላይ ያለነው ። ለዚህ ነው በየሰበቡ ሕይወት የሚታክተን ። ለዚህ ነው መኖር ትግል ፣ አብሮነት መተናነቅ የሚሆንብን ( የሆነብን ) ። የቤተልሔም ሸረፈዲን ” ቻው ” ለአንድ ተፈቃሪ ወንድ የተሰራም ቢሆን ሀሳቡ ግን እዚህ ድረስም የሚመጣ ነው ። ናቲ ” ቃሉ ከዜማው ጋር ነው የመጣው ” ያለውና ራሷን ድምጻዊቷን አስለቅሶ የተገለጠው ” ቻው ” ገና ብዙውን ልብ የሚነካ ስራ ይሆናል ።

” ልቤን ” ን ላልወደው አስቤ ነበረ መሰለኝ ። የእድሜም ፣ የፍላጎትም ጉዳይ ሆኖ ፈጠን ላሉ ምቶች አልደነግጥ ሆኖ ይሆናል እንጂ ምን ሆኜ ነው ዜማው ፣ ምቱ ፣ በተለይ የድምጻዊቷ አዘፋፈን ከፍ ብሎ የታየበትን ይህን ስራ ” ይቆየኝ ” ያልኩት ? ባልወደውና ደጋግሜ ባልሰማው ይቆጨኝ ነበር ። ( ለነገሩ ካልወደድኩት ለምን ይቆጨኛል ? ) ” ደስተኛ ” ርዕስና ሀሳቡ ደስተኛ ካልሆነች ፣ ” አልወድሽም ” ከተባለችና ከተገፋች ገጸባህሪ የተገኘ ነው ። ” ቢከፋም ፣ ቢለማም ባለኝ ደስተኛ ነኝ ” ትላለች ። ” አልወድሽም ” ተብላና ” ብትጎዘጉዝ አበባ ዛሬ አይረባ ” ያለች ሴት ራሷን ማታለል ሳይሆን ” ቢከፋም ፣ ቢለማም ባለኝ ደስተኛ ነኝ ” ስትል ካዋጣትና ከተቻላት ያድርግላት ። ከእሷ እንባና የልብ ስብራት ምን ጉዳይ አለን ? ብቻ ከአፏ ሳይሆን ከልቧ ይሁን ።

” እንደ ውሀ መውረድ ፣ እንደ ጸሐይ መውጣት
እንደ ጊዜው መክነፍ ፣ እንደ አሸዋ መብዛት
እውነታ መሆኑን ቅንጣት ሳልጠረጥር
እኔስ አምነዋለሁ የልብህን ፍቅር ”

ያለችበት ” አካልዬ ” ለረጋ ያለ ሙዚቃ አፍቃሪ ይሁነኝ ተብሎ የተቀመረ ስራ ነው ። በምርጤነት ከተቀበልኳቸው መካከል አንዱ ነው ።

አንደኛው ሙዚቃ አስተያየት መስጫ ውስጥ ገብቼ ሳነብ ” የዚህ አልበም ትልቁ ችግሩ ውስጡ ያሉት ዘፈኖች 10 ብቻ መሆናቸው ነው ” ሲል ” አድናቆቱን ” ገልጿል ። እኔም እንደዚያ ሆኖ ይሰማኛል ። ከአስሩ ሰባቱን ስራዎች በልዩ ሁኔታ ወድጃቸዋለሁ ። አንዱ የዋለልኩበትና ሁለቱ ደግሞ ልብ ያልሰጠኋቸው ናቸው ። ይህ በአንድ አለበም ውስጥ ከበቂ በላይ ስኬታማነት ነው ። ከብዙ ዓመት በኋላ ተሟልቶ ያገኙሁት ምርጤ ነው ” ደስተኛ ” አልበም ።

እዚህ አልበም ላይ ያለኝ አንድ ( ግላዊ ) ቅሬታ አስሩም ስራዎች የተቃራኒ ጾታ ፍቅር ላይ ብቻ ያተኮሩ መሆናቸው ነው ። እንዳይሆኑ የሚከለክል ደንብ የለም ። ፕሮዲዩሰሮቹ የቤተልሔምን እድሜና የፍቅር ጊዜዋን አስበው ያደረጉት ሊሆን ይችላል ። ያም ቢሆን በዚህ ውጥንቅጡ የወጣ የመከራ ጊዜ ፣ በብዙ ሰው ሰራሽና የአስተሳሰብ ሰንሰለት እግር ከወርች ታስረን መሔጃ ባጣንበት ዘመንና ሀገር ፣ ላለንበት ጊዜ ፣ ለስሜታችን ፣ ለህመማችን ፣ ለሰለለው ተስፋችን የሚሆን አንድ ስራ ልናጣ አይገባም ብዬ አስባለሁ ። ናቲና ምህረተአብ ለራሄል ጌቱ እንደሰጧት ” ያገሬ ሰው ” ያለ ስራ ቢመርቁልን እንዴት መልካም ነበረ ?

ከቀናት በፊት አስቴር አወቀ ( በድጋሚ ስራዎቿም ቢሆን ) በትንሿ ቤተልሔም ሸረፈዲን ላይ ተደርባ አልበሟን መልቀቋ አስፈርቶኝ ነበረ ። ይህን የመሰለ አልበም ፣ የ4 ዓመት የሚነገርና የማይነገር እልህ አስጨራሽ ድካም መና እንዳይቀር ሰግቼ ነበረ ። ስጋቴ ስጋት ብቻ ሆኖ ቀርቷል ። ቤተልሔም የዋርካው ጥላ ሳያርፍባት አልፋለች ። ገና ገና ትቀጥላለች ፤ ትቀጣጠላለች ።


Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2