#Ethiopia | የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው፣ በአሜሪካ መንግስት ምክትል ረዳት ፀሐፊ ሚስተር ማርክ ትራውንተር ሚቼል የተመራውን ልዑክ በመቀበል የኢትዮጵያን የኢነርጂ ዘርፍ ለማዘመን እና በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የትብብር ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ ውይይት አካሂደዋል።
በውይይቱ የኤሌክትሪክ ስርጭት መረብ (Grid) ማዘመን፣ ዲጂታል ሽግግር፣ ስማርት ቆጣሪዎችን ማስፋፋት፣ ንጹህ ኢነርጂ፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች፣ የኢንቨስትመንት እድሎች እና የአቅም ግንባታን ጨምሮ በርካታ ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ምክክር ተካሂዷል።
እንዲሁም የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ስርጭት ሥርዓት አስተማማኝነትና ዘላቂነት ለማሳደግ፣ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማስፋፋት፣ የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገትና ኢንዱስትሪያላይዜሽን ለመደገፍ እና ዘላቂ ልማትን ለማፋጠን የሚያስችሉ ተግባራዊ የትብብር አቅጣጫዎች ተዳሰዋል።
ኢንጂነር ጌቱ ገረመው በውይይቱ ላይ እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዘመናዊ፣ ጠንካራና ለደንበኞች ምቹ የሆነ ተቋም ለመገንባት ፈጠራን፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን እና ስትራቴጂያዊ አጋርነቶችን በማጠናከር በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል ያለው የረጅም ዓመታት የትብብር ግንኙነት ወደ ተጨባጭ የልማት ፕሮጀክቶች እንደሚሸጋገር መተማመናቸውን ገልጸዋል።
የአሜሪካ ልዑክ በበኩሉ፣ በኢትዮጵያ የኢነርጂ ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ የዘመናዊነት ሥራዎችን በማድነቅ፣ በጋራ በመሥራት የኢትዮጵያን የኃይል ዘርፍ ለማጠናከር ያለውን ፍላጎት ገልጿል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትም የአገሪቱን የኢነርጂ ሽግግር ለማፋጠን፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ተደራሽ፣ አስተማማኝና ዘላቂ ለማድረግ ከዓለም አቀፍ አጋር ተቋማት ጋር ያለውን ስትራቴጂያዊ ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጧል።
በማጠቃለያው፣ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው ለሚስተር ማርክ ትራውንተር ሚቼል እና ለመላው ልዑካን ለጉብኝታቸውና ለገንቢ ውይይታቸው ምስጋና አቅርበው፣ የሁለቱ ወገኖች ትብብር እየተጠናከረ በሄደ ቁጥር የኢትዮጵያን የኢነርጂ ሽግግር የሚያፋጥኑ አዳዲስ እድሎች እንደሚፈጠሩ እምነታቸውን ገልጸዋል።
Source: GetuTemesgen









No comments yet.