“18 ሰው ቀርቶብናል፥ እናትና ልጅም ይገኙበታል፥ ለአዘጋጆቹ ወዲያው አሳውቀናል” – የፕሮጀክቱ መስራች

- Advertisement -
Sidebar AD

ለጎቲያ ካፕ ወደ ስዊዲን ከሄዱ የኢትዮጵያ ቡድኖች መካከል ደብል ፓስ የእግር ኳስ ፕሮጀክት አንዱ ነው፤ ከቀሩት ተጫዋቾች አብዛኞቹ ከዚህ ስብስብስ የተገኙ በመሆናቸው ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጠን የፕሮጀክቱ መስራች ታዲዮስ ተክሉ ጋር ደውለን ተከታዩን ቆይታ አድርገናል፥ እነሆ፦

ታዲዮስ ስለ ትብብርህ በቅድሚያ እናመሰግናለን፤ ስለራስህና ስለ ፕሮጀክታችሁ በማስተዋወቅ እንጀምር እስኪ?

“ጉዳዩን ለማጥራት ስለደወልክልኝ ታምሩ እኔም አመሰግናለሁ፤ ታዲዮስ ተክሉ እባለሁ፤ የቀድሞ ተጫዋች የአሁን አሰልጣኝ ነኝ፤ ከጫካ ሜዳ ፕሮጀክት ጀምሮ የኢትዮጵያ ቡና፣ ንግድ ባንክና ኤሌክትሪክ ታዳጊ ቡድኖችን አሰልጥኛለሁ፤ የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆኜም በሴካፋ ተሳትፌያለሁ፤ አሁን ደግሞ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ሴቶች ቡድንን አሰለጥናለሁ፤ በተጨማሪ የደብል ፓስ ፕሮጀክት መስራችና ዋና አሰልጣኝ ነኝ፤ ይህ ፕሮጀክት ከተቋቋመ ዘጠኝ አመት ሆኖታል፤ በአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ስር ተመዝግበን በከተማው ከ20 አመት በታች ውድድር ላይ እንሳተፋለን”

የስዊዲን ጎቲያ ካፕ እድልን እንዴት አገኛችሁ?

“በራሳችን ጥረት ተፃፅፈን ነው እድሉን ያገኘነው፤ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ ነው የተሳተፍነው፤ ከዚህ ቀደም ዴንማርክ ላይም ውድድር አድርገናል”

እስኪ ስለ ስዊዲን ጉዟችሁ አጫውተን

“18 ተጫዋቾችንና 4 የአሰልጣኝ አባላትን በጥቅሉ 22 ልዑካንን ይዘን ነው የሄድነው፤ በውድድሩም ጥሩ ተሳትፎ ነበረን”

22 ሆናችሁ ሄዳችሁ ስንት ሆናችሁ ተመለሳችሁ?

“1 ተጫዋች( የዘማሪ አሸናፊ ገብረ ማርያም ልጅ ፣ ሚካኤል አሸናፊ ) ና 3 የአሰልጣኝ አባላት በአጠቃላይ 4 ሰዎች ብቻ ነው ወደ አዲስ አበባ የተመለሰው፤ 18ቱ አልመጡም”

ይህ እንዴት ሊፈጠር ቻለ?

“የሁላችንም መመለሻ ቀን ውድድሩ ከተጠናቀቀ ከሁለት ቀን በኋላ ነበር፤ ሆኖም የአንዱ ታዳጊ ተጫዋች የቅርብ ቤተሰብ ሰርግ ሀምሌ 12 ስለነበር ወላጆቹ ቶሎ ቢመጣልን አሉን፤ በእድሜው ምክንያት ብቻውን መላክ ስለማንችል እኔና ሁለት የአሰልጣኝ አባላት እንዲሁም ተጫዋቹን ጨምሮ አራት ሆነን ትኬታችንን አስተካክለን በፍፃሜው ቀን ቅዳሜ ሀምሌ 11/2018(ጁላይ 18/2026) ወደ አዲስ አበባ ተመለስን፤ ቀሪዎቹ 18ቱ ሰኞ ሀምሌ 13 ነበር የመመለሻ ቀናቸው፤ እኛ አዲስ አበባ ሳንደርስ ለትራንዚት በቆየንበት ኳታር ሆነን ግን ተጫዋቾቹ ቡድናችን ካረፈበት ትምህርት ቤት ሳያሳውቁ እንደወጡ ተነገረን”

ከዛ ምን አደረጋችሁ?

“ወዲያው ለአዘጋጆቹ አሳወቅናቸው፤ እነሱም ለመረጃው አመስግነውን ለሚመለከተው የፀጥታ አካል እንሳውቃለን አሉን፤ አዲስ አበባ ከደረስን በኋላ ድጋሚ አንዷ የቡድን መሪ ጋር ስደውል እንደማይመለሱ፥ ተጫዋቾቹንም ስዊዲን የሚኖሩ ቤተሰብና ዘመዶቻቸው እንደወሰዷቸው ነገረችን፤ ኢትዮጵያ ያሉ ወላጆችንም ጠየቅን፤ ልጆቹ ያሉበትን ቦታ ለመናገር ፈቃደኛ አልሆኑም፤ ይህንንም ለአዘጋጆቹ በድጋሚ አሳውቀናል፤ ከ10 ቀን በኋላ ዜናውን አወጡት”

ይህ እንዳይከሰት ቅድሚያ ዝግጅት አላደረጋችሁም?

“በደንብ አድርገናል፤ ውል አዘጋጅተን የሁሉንም ተጫዋቾች ወላጆች አስፈርመናል፤ ስዊዲን ከደረስን በኋላም የሁሉም ተጫዋቾች ፓስፖርት እኔ ጋር ነበር፤ ሆኖም እኔ ቀድሜ መመለስ ስለነበረብኝ ፓስፖርቱን ለቡድን መሪ ሰጠሁ፤ ተያይዘው ቀሩ፤ ውስጥ ውስጡን በደንብ ተዘጋጅተውበት ነበር”

ለመሆኑ ወጪያችሁን የሸፈነው ማነው?

“የተጫዋቾቹን የጉዞ ወጪ የቻሉት ወላጆቻቸው ናቸው”

ምን ያህል ከፈሉ?

” ለስልጠና፣ ለጉዞና ለተለያዩ አቅርቦቶች እያንዳንዳቸው 300ሺህ ብር ከፍለዋል፤ የተሻለ አቅም ያላቸው ደግሞ 400ሺህ ብር ከፍለው አግዘውናል”

ለምን 400ሺህ ብር?

“የመክፈል አቅም የሌላቸውን ሶስት ያህል ተጫዋቾችን ይዘን ሄደናል፤ የእነሱን ወጪ ደግሞ እኛና አቅም ያላቸው ወላጆች ሸፍነናል፤ ወላጆቹ ከ300ሺህ ብር በተጨማሪ 100ሺህ ብር እየጨመሩ 400ሺህ ብር እየከፈሉ አቅም የሌላቸው ተጫዋቾች እንዲሄዱ አግዘውናል”

ከተጫዋቾች በተጨማሪ ወላጆችስ ሄደዋል?

“አዎ ሁለት ተጫዋቾች ከእናቶቻቸው ጋር አብረው ወደ ስዊዲን ሄደዋል”

እና ተመለሱ?

“ሁለቱም ተጫዋቾችም ሆኑ እናቶቻቸው አልተመለሱም”

ተጓዥ ተጫዋቾች ከእግርኳስ ጋር ያላቸው ግንኙነትና ችሎታ ደካማ የሆኑ፥ የባለሀብትና የባለስልጣን ልጆች ናቸው ይባላል እውነት ነው?

“ፕሮጀክታችን በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንና በፊፋ ኮኔክት የተመዘገበ ነው፤ ሆኖም እድሜያቸው ከ16 አመት በታች ስለሆኑ ችሎታ ላይ ብቻ የተመሰረተ ምልመላ አናደርግም፤ ይህን መሰል አለም አቀፍ ውድድር ላይ ስንሳተፍ ደግሞ ቪዛ ለማግኘት አንዱ መስፈርት የወላጆቹ ኢኮኖሚያዊ አቅም ይታያል፤ ስለዚህ የባለሀብትም የባለስልጣንም ልጆች ይኖሩናል፤ ከቀሩት ውስጥ ግን የባለስልጣን ልጅ የለም”

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በተጫዋቾቹ መጥፋት አዝኛለሁ ሆኖም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አባላት አይደሉም ብሎ መግለጫ አውጥቷል፤ ምን ትላለህ?

“እንዳልኩህ በራሳችን ጥረት ነው ተሳትፎውን ያገኘነው፤ ከብሄራዊ ቡድን ጋርም አይገናኝም፤ በተፈጠረው ነገር ዋነኛ ተጎጂዎችም እኛ ነን፤ ስማችን ላይ ትልቅ አሉታዊ ተፅዕኖ አለው፤ በጣም አዝነናል”

በድጋሚ ለትብብርህ ላመስግንህና የመጨረሻ ጥያቄ ላንሳ፥ የቡድኑ ፎቶ ላይ አንድ ህፃን ልጅ ይታያል፤ ተጫዋች ነው?

“ኸረ አይደለም፤ የእኔ ልጅ ነው፤ ገና ስድስት አመቱ ነው፤ አብረን ሄደን አብረን ተመልሰናል”

★ ማስታወሻ፦ ከደብል ፓስ ፕሮጀክት በተጨማሪ በአሰልጣኝ እድሉ ደረጄ የሚመራው ኢዲዋይ እና ዳን አቢሲኒያ የተባሉ ቡድኖች በስዊዲን ጎቲያ ካፕ ተሳትፈዋል፤ እነሱም ማብራሪያ እንዲሰጡን ጠይቀን ምላሻቸውን እየጠበቅን ነው

(ታምሩ ዓለሙ)





Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2