በትግራይ ክልል የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በወረቀት እየተሰጠ ነው

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | በትግራይ ክልል ለሚገኙ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የሚሰጠው የሀገር አቀፍ ማጠናቀቂያ ፈተና በወረቀት በአዲስ አበባ፣ በመቐለ እና በአክሱም ዩኒቨርሲቲዎች በተዘጋጁ ማዕከላት እየተሰጠ መሆኑ ተገልጿል።

የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሕይወት በአዲስ አበባ የሚገኘውን የፈተና ማዕከል ጎብኝተው፣ መንግሥት ባደረገው ዝግጅት መሰረት የትግራይ ተማሪዎች በተለያዩ ማዕከላት ፈተናቸውን በሰላም መጀመራቸውን ገልጸዋል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፣ በአክሱም፣ በመቐለና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች ከ15 ሺህ በላይ ተማሪዎች በወረቀት የሚሰጠውን ፈተና እየወሰዱ ሲሆን፣ በክልሉ በሚገኙ አራት ዩኒቨርሲቲዎች በበይነ መረብ (ኦንላይን) የተሰጠው ፈተናም በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

ፕሮፌሰር ክንደያ በሁሉም የፈተና ማዕከላት የሚፈተኑ ተማሪዎች በመረጋጋት ፈተናቸውን እንዲወስዱ በመመኘት፣ መልካም ውጤት እንዲያስመዘግቡ ምኞታቸውን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ፈይሳ፣ ፈተናው መጀመሩ የክልሉ ወጣቶች ትምህርታቸውን በመቀጠል የወደፊት ዕድላቸውን እንዲያሻሽሉ ጠቃሚ እንደሆነ ገልጸዋል። እንዲሁም ተማሪዎች ያለምንም እንግልትና ስጋት ፈተናቸውን እንዲወስዱ የፀጥታ አካላትና የፈተና አስተባባሪዎች የተቀናጀ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከ30 ሺህ በላይ የትግራይ ክልል ተማሪዎች በወረቀትና በበይነ መረብ በአዲስ አበባ፣ በመቐለ እና በአክሱም ዩኒቨርሲቲዎች ፈተናቸውን እየወሰዱ መሆኑ ተገልጿል።






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: