አምስት ቋንቋዎች የፌዴራል የሥራ ቋንቋ እንዲሆኑ ምክረ ሀሳብ ከተሳታፊዎች ቀረበ።

- Advertisement -
Sidebar AD

👉 የውጭ ቋንቋዎች “የፌዴራል የሥራ ቋንቋ” እንዲሆኑ ምክረ ሀሳብ ቀርቦ “የኛን ቋንቋዎች ያጠፋል” በሚል አከራካሪ ሆኗል።

በምክክር ጉባዔው በ10 እና 50 ሰዎች ደረጃ የተደራጁ ንዑሳን ቡድኖች የተነጋሩባቸው የአጀንዳ ምክረ ሀሳቦች 250 ሰዎችን ለሚይዘው “ስልታዊ” ቡድን የመመራት ሂደት ላይ ደርሰዋል።

ጉባያተኞቹ ከሚመክሩባቸው 8 አጀንዳዎች መካከል “የሀገር ግንባታ” አንዱ ሲሆን፣ በዚሁ አጀንዳ ላይ በ10 እና 50 ሰዎች የተደራጁ ንዑሳን ቡድኖች በውይይታቸው ያቀረቧቸውን ዋና ዋና ምክረ ሀሳቦችን ጉዳዩን በጥልቅ የተከታተሉት የቲክቫህ ኢትዮጵያ ምንጭና ከሰላም ተፅዕኖ ፈጣሪ ኢትዮጵያውያን ማህበር የተወከሉት አቶ ከበደ ፉንዳ አብራርተዋል።

እኝሁ አካላት እንደገለጹት በዚሁ አጀንዳ፦
– ሀገር የማን ናት ? የብሔር ወይስ የዜጋ ?
– የኢትዮጵያ ማንነት ዜግነትን፣ ብሔርን፣ ወይስ መድብለ ብሔራዊ ፌዴራላዊ ማንትነን መሰረት ያደርግ፣
– ከ”እኛ” እና “እነርሱ” ከሚለው ከፋፋይ ትርክት እንዴት ወደ እኩልነትና የጋራ ተጠቃሚነት ስሜት እንደሚመጣ፣
– የሚጋጩ ታሪኮች እንዴት እንደሚታረቁ፣
– የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት እንዴት እንደሚገመገም፣
– በኢትዮጵያ ባንዲራ ያለው አርማ እንዲወጣና በእርግብና በሌሎች ምልክቶች እንዲተካ፣
– በፌዴራል የሥራ ቋንቋ ጉዳይ እና በሌሎች ጉዳዮች የተለያዩ ምክረ ሀሳቦች ቀርበውበታል።

የፌዴራል የሥራ ቋንቋ ጉዳይ በሚመለከት ስለቀረቡ ምክረ ሀሳቦች ማብራሪያ የሰጡን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ታማኝ ምንጭ፣ ” ‘አማርኛ በብዙ ኢትዮጵያውያን የሚነገር ከመሆኑ አንፃር አሁን ያለው የፌዴራል የሥራ ቋንቋ መሆኑን ይዞ ይቀጥል፤ አማርኛ እና ኦሮምኛ የፌዴራል ቋንቋዎች ይሁኑ’ ” የሚሉ ምክረ ሀሳቦች መቅረባቸውን ተናግረዋል።

እንዲሁም ፦
° አማርኛ፣
° ኦሮምኛ፣
° ትግርኛ፣
° አፋርኛ፣
° ሶማሊኛ የፌዴራሉ የሥራ ቋንቋ ይሁኑ የሚሉ ሀሳቦች መቅረባቸውን ገልጸው፣ ” ‘አማርኛ ብሔራዊ ቋንቋ ሆኖ ሌሎቹ ደግሞ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ ይሁኑ’ የሚልም ሀሳብ አለ ” ብለዋል።

• እንግሊዝኛ፣
• አረብኛ፣
• ፈረንሳይኛ፣
• ቻይንኛ የውጭ ሀገራት ቋንቋዎች “በትምህርት ሥርዓት ውስጥ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ” ቢካተቱ፣ “የፌዴራል የሥራ ቋንቋዎች ቢሆኑ” የሚሉ ሀሳቦች ቀርቦ፣ በሌላ በኩል ደግሞ “የኛን ቋንቋ ያጠፋል” በሚል አከራካሪ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከሥራ እድል አኳያ እንዲሁም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረትና የሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ ከመሆኗ አንፃር፣ “ፈረንሳይኛ፣ ስዋህሊኛ፣ እንግሊዝኛ ቋንቋዎች በካሪኩለም ተካተው ኢትዮጵያውያን የሚማሩበት መሆን አለበት” የሚል ሀሳብ መቅረቡንም ምንጫችን ገልጸዋል።

የክልሎች የቋንቋ አጠቃቀምን በተመለከተ፥ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ ሊሆኑ ይገባል ከሚባሉት መካከል ቢያንስ ሁለቱን ክልሎቹ ተጨማሪ የክልሉ የሥራ ቋንቋ አድርገው እንዲጠቀሙ ከተሳታፊዎች ምክረ ሀሳብ መሰንዘሩንም አስረድተዋል።

የፌዴራል የሥራ ቋንቋዎች መሆን ያለባቸው የሚመረጡት በክልሎቹ የህዝብ ቁጥር መሰረት እንዲሆን መጠየቁንም ያስረዱት ምንጫችን፣ የቀረቡት ምክረ ሀሳቦች ገና በቀጣዮቹ ቡድኖች ጭምር ምክክር እንደሚደረግባቸውና ገና ድምዳሜ ላይ እንዳልተደረሰባቸው አስገንዝበዋል።

የሀገር ግንባታን በተመለከተው አጀንዳ የተነሱ ሀሳቦች እየተደራጁ መሆኑን የነገሩን የሰላም ተፅዕኖ ፈጣሪ ኢትዮጵያውያን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ከበደ ፉንዳ በበኩላቸው፣ የሥራ ቋንቋን በተመለከተ ከአማርኛ በተጨማሪ ያሉት ቋንቋዎችም እንዲመረጡ ምክረ ሀሳብ መቅረቡን ገልጸዋል።

የተነሱት ምክረ ሀሳቦች ገና በ250 እና 500 ቡድኖች እንዲሁም በ4,ዐዐ0 ተሳታፊዎች የሚመከርባቸው መሆናቸውን ተሳታፊዎቹ አስምረውበታል።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን ዓርዓያ፣ ” ወገኖቻችን ቅርብ ለቅርብ ሆነው እየተከባበሩ እየተነጋገሩ ነው ” ብለዋል።

“በሚቀጥለው ፌዝ መጋጨቶች ይጠበቃሉ። ምክንያቱም ሁላችንም ይዘን የመጣነውን ነው እዚህ የምናራግፈው። ስለዚህ ይሄ የመደማመጥ ፌዝ ነው” ያሉት መስፍን (ፕ/ር)፣ የመኳረፍና መከፋፈል ነገሮች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ከዚህ ቀደም መናገራቸውን አስታውሰው፣ ” ነገር ግን እንደተፈራው አይደለም ” ብለዋል።


Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2