የዓለም የጸሐፍት ድርጅት (WOW) ዓለም አቀፍ ጉባኤ ዛሬ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

- Advertisement -
Sidebar AD

ዕዝራ እጅጉ

#Ethiopia | በኢትዮጵያውያን ደራሲያን እና በውጭ አገር የሥነ-ጽሑፍ ባለሙያዎች ተሳትፎ የሚካሄደው የዓለም የጸሐፍት ድርጅት (WOW) ዓለም አቀፍ ጉባኤ ዛሬ ሐምሌ 22 ቀን 2018 ዓ.ም. ከ10:00 ሰዓት ጀምሮ በአዲስ አበባ ኢሊሊ ሆቴል ይካሄዳል።

ጉባኤው “Africa in Shaping a Common Future” በሚል መሪ ቃል የሚካሄድ ሲሆን፣ በአፍሪካ ሥነ-ጽሑፍ፣ ባህላዊ እሴቶች እና የደራሲያን ዓለም አቀፍ ትብብር ዙሪያ የሚያተኩሩ ርዕሰ ጉዳዮች ይቀርባሉ።

በመድረኩ ላይ በአፍሪካ ሥነ-ጽሑፍ ላይ ጥናት ያካሄዱት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር አቢይ ዳንኤል የጥናት ወረቀት እንደሚያቀርቡ ሲገለጽ፣ ፀሐፌ ተውኔት አያልነህ ሙላቱም ከዋና የጽሑፍ አቅራቢዎች መካከል ይገኛሉ።

የድርጅቱ ፕሬዝዳንት ማርጋሪታ አል ለጉባኤው በተለይ ወደ አዲስ አበባ የመጡ ሲሆን፣ የጉባኤው ሁሉም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸው ተገልጿል።

ጉባኤው በኢትዮጵያ መካሄዱ የኢትዮጵያ ደራሲያን ከዓለም አቀፍ የሥነ-ጽሑፍ ማኅበረሰብ ጋር ያላቸውን ትስስር በማጠናከር የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይጠበቃል።

በመጽሐፍ ዝግጅትና ሥነ-ጽሑፍ ሥራ ላይ የተሰማራው “ተወዳጅ ሚዲያ እና ኮምዩኒኬሽን” መሥራች ዕዝራ እጅጉን ጨምሮ የዝግጅት ኮሚቴው አባላትም በጉባኤው ይሳተፋሉ ተብሏል።

ስለ WOW

የዓለም የጸሐፍት ድርጅት (WOW) ዓለም አቀፍ ደራሲያንን ለማገናኘት፣ የሥነ-ጽሑፍ ሥራዎችን ለማበረታታት እና በባህሎች መካከል ውይይትን ለማጠናከር የተቋቋመ ዓለም አቀፍ ማኅበር ነው። ዋና መሥሪያ ቤቱ በሞስኮ የሚገኝ ሲሆን፣ በፕሬዝዳንት ማርጋሪታ አል ይመራል።

የድርጅቱ የምሥረታ ሀሳብ በ2019 በባኩ፣ አዘርባጃን የቀረበ ሲሆን፣ በ2023 በካይሮ፣ ግብፅ በስምምነት ሰነድ ተመስርቶ በዚያው ዓመት በይፋ ተመዝግቧል። የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ጉባኤውም በ2024 በዓቡጃ፣ ናይጄሪያ ተካሂዶ ነበር።

WOW በአሁኑ ጊዜ አባልነቱን በተለያዩ አገሮች እያስፋፋ ሲሆን፣ የፓናል ውይይቶችን፣ የልጆች የሥነ-ጽሑፍ መድረኮችን እና የጋራ የትርጉም ፕሮጀክቶችን በማካሄድ የዓለም አቀፍ የሥነ-ጽሑፍ ትብብርን ለማጠናከር እየሠራ ነው።


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1