”አቡነ ቄርሎስ ግብፃዊ ናቸው፤ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር የለም፡፡ እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡” ብፁዕ

- Advertisement -
Sidebar AD

”አቡነ ቄርሎስ ግብፃዊ ናቸው፤ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር የለም፡፡ እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡” ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ

ሐምሌ ፳፪ ቀን ፲፱፳፰ ፤ ፭፡፲፭ ሰዓት

#Ethiopia | ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ቁመታቸው ረዘም፣ ፊታቸው ዘለግ ያለ፣ መልካቸው ጠየም ያለ፣ አዋቂነታቸው እና ትህትናቸው ከገፃቸው የሚነበብ ሲሆን በዚህ ጊዜ ለብሰውት የነበረው ልብስ ጵጵስና ጥቁር ካባ ያውም በጭቃ የተበከለ ነበር ፡፡

በዚህ ሁኔታ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ወደ ችሎት ቀረቡ፡፡ ለፍርድም የተሰየሙት ዳኞች ሦስት ሲሆኑ እነዚህም የጣሊያኖች የጦር ሹማምንት ናቸው፡፡ የመካከለኛው ዳኛ ኮሎኔል ነበር፡፡ የቀረበባቸውም ወንጀል ሕዝብ ቀስቅሰዋል፣ እራስዎም ዐምፀዋል፣ ሌሎችንም እንዲያምፁ አድርገዋል የሚል ነበር፡፡ ዳኛውም “ካህናቱም ሆኑ የቤተ-ክህነት ባለሥልጣኖች ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ቄርሎስም የኢጣሊያንን መንግሥት ገዢነት አምነው አሜን ብለው ሲቀበሉ እርስዎ ለምን ዐመፁ? ለምን ብቻዋን አፈንጋጭ ሆኑ?” ሲል ጠየቃቸው፡፡

አቡነ ጴጥሮስም የሚከተለውን መለሱ፡፡ “አቡነ ቄርሎስ ግብፃዊ ናቸው፤ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር የለም፡፡ እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ ሐላፊነትም ያለብኝ የቤተ ክርስቲያን አባት ነኝ፡፡ ስለዚህ ስለ ሀገሬና ስለ ቤተክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ፡፡ ከዚህ በቀር ለእናንተ ችሎት የማቀርበው ነገር የለኝም፡፡ ለፈጣሪዬ ብቻ የምናገረውን እናገራለሁ፡፡ እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ ዐውቃለሁ፡፡ ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ፡፡ ግን ተከታዮቼን አትንኩ” አሉ፡፡

“ይህንንም ብለው በጥይት ተደብድበው ሲገደሉ እንዲያይ ተጋብዞ ለተሰበሰበው ሕዝብ የሚከተለውን ሕያው መልእክት አስተላለፉ “አረማዊ የሆነው የፋሺስት መንግሥት ቤተ-ክርስቲያንን ለማቃጠል፣ ሕዝበ ክርስቲያንን ለመግደል፣ ሃይማኖትን ለማጥፋት፣ ታሪካችንን ለማበላሸት የመጣ ነው እንጂ በጎ ለመሥራት እውነተኛ ፍርድ ለመስጠት ስላልመጣ ለዚህ ለግፈኛ አትገዙ፡፡ ስለ ውድ ሀገራችሁ፣ ስለ ቀናች ሃይማኖታችሁ ተከላከሉ፡፡ ነፃነታችሁ ከሚረክስ ሙታችሁ ስማችሁ ቢቀደስ ታላቅ ዋጋ ያለው ክብር ታገኛላችሁ፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዚህ ለጠላት እንዳይገዛ አውግዣለሁ፤ የኢትዮጵያ መሬት ጠላትን ብትቀበል የተረገመች ትሁን፡፡ በፈጣሪዬ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተገዘተች ትሁን፡፡”

ወዲያው የሞታቸው ፍርድ ሲሰማ ሕዝቡ በኢጣልያ የእጅ ሰላምታ ዓይነት እጁን እንዲያነሳ ታዘዘ ፡፡ በዚያን ጊዜ አቡነ ጴጥሮስ የሞታቸው ሰዓት መድረሱን ዐውቀው ሰዓታቸውን ከኪሳቸው አውጥተው ተመለከቱ ፡፡ሐምሌ 22 ሰዓቱም 5፡15 ነበር ፡፡ በዚህ ጊዜ ሁሉ ምንም ፍርሃት አይታይባቸውም ነበር፡፡ የሞታቸውን ፍርድ ያነብ የነበረው ኢጣሊያዊ ዳኛ ግን ይንቀጠቀጥ ነበር ፡፡ ታላቅ ፍርሃትም በፊቱ ላይ ይታይ ነበር፡፡

(ከታሪክ ማህደር አጠር ተደርጎ የቀረበ)

በያፌት ገ/ህይወት

Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)

#getutemesgen #getu


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1