ዓለም አቀፍ የሬንጀሮች ቀን “ሬንጀሮች፡- ተለዋዋጭ ለሆነችው ፕላኔት ጠባቂዎች” በሚል መሪ ቃል ተከበረ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | አዲስ አበባ፦ የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የሬንጀሮች ቀን “ሬንጀሮች፡- ተለዋዋጭ ለሆነችው ፕላኔት ጠባቂዎች (Rangers: Guardians of a Changing Planet)” በሚል መሪ ቃል ተከብሯል።

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ባስተላለፈው መልዕክት፣ የዓለም ማህበረሰብ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በአካባቢ ብክለት፣ በብዝሃ ሕይወት መመናመንና በአዳዲስ የጤና ስጋቶች እየተፈተነ ባለበት ወቅት ሬንጀሮች የተፈጥሮ ሀብትንና የዱር ሕይወትን በመጠበቅ ለፕላኔታችን ሕልውና የማይተካ አስተዋፅኦ እያበረከቱ መሆናቸውን ገልጿል።

በመልዕክቱ የኢትዮጵያ ሬንጀሮች ንፁህ ውሃ፣ ለም አፈር፣ የተረጋጋ ሥነ-ምህዳር እንዲሁም የዱር እንስሳትና ዕፅዋት ለአሁኑና ለሚቀጥለው ትውልድ እንዲጠበቁ በትጋት እየሠሩ እንደሚገኙ ተጠቅሷል። በተለይም በጥበቃ ቦታዎች ሕይወታቸውን ለአደጋ በማጋለጥ የሚያከናውኑት ተልዕኮ ከፍተኛ ክብርና ዕውቅና እንደሚገባው ተመልክቷል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ተቋሙ የሬንጀሮችን የሙያ አቅም ለማጠናከር፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የተጠቀመ የጥበቃ ሥርዓት ለማስፋፋት፣ ክህሎትና ዕውቀታቸውን ለማሳደግ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሬንጀሮች ማህበር ይበልጥ እንዲጠናከር በቀጣይነት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ አስታውቀዋል።

በመጨረሻም ባለስልጣኑ በተፈጥሮ ጥበቃ ተልዕኮ ላይ ለሚገኙ ሁሉም ሬንጀሮች ምስጋና እያቀረበ፣ ለዱር ሕይወት ሕልውና ሲሉ ሕይወታቸውን ለከፈሉና አካላቸውን ለገበሩ ሬንጀሮችና የዘርፉ ባለሙያዎች ዘላለማዊ ክብር እንደሚገባቸው ገልጿል።


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: