«ከለውጡ በኋላ የነበረውን የመታፈን ስሜት ለማናፈስ በተደረገው ጥረት ውስጥ የተቀላቀሉ ቢምቢዎች ነበሩ»- ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አ…

- Advertisement -
Sidebar AD
«ከለውጡ በኋላ የነበረውን የመታፈን ስሜት ለማናፈስ በተደረገው ጥረት ውስጥ የተቀላቀሉ ቢምቢዎች ነበሩ»– ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ ጉዞንና ከዚያ በኋላ በሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ የታዩትን ኩነቶች አስመልክተው ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ  በሰጡት ማብራሪያ፣ የዐማራ ሕዝብ እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ለለውጥና ለዕድገት ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረጉን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፣ ከለውጡ ማግሥት የነበረው ጉዞ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በከፍተኛ ተስፋ የተሞላበት፣ «በዚህ ለውጥ እሠራለሁ፣ አተርፋለሁ፣ ሀገር አጠናለሁ» የሚል ሕልም በሰፊው የተገለጸበት ወቅት ነበር። ከለውጡ በፊት በነበረው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሥርዓት ውስጥ የመዘጋትና የመታፈን ምልክቶች እንደነበሩ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የተዘጋን ቤት መስኮት ከፍቶ እንደማናፈስ ሁሉ ፖለቲካውንም ማናፈስ አስፈላጊ ነበር ብለዋል።
ሆኖም መስኮቶች ሲከፈቱ ንጹሕ አየር ብቻ ሳይሆን «ቢምቢዎችና ትንኞችም» አብረው እንደሚገቡ በመግለጽ፣ በፖለቲካው ምህዳር መከፈት ምክንያት አጋጣሚውን በመጠቀም ሁኔታዎችን ወደ ሥጋትና ድንግዝግዝነት ለመቀየር የሞከሩ አካላት እንደነበሩ አስረድተዋል።
«ቢምቢ በሳይዟ በጣም ትንሽ ናት፤ ነገር ግን ድምፅ በማሰማት እንዳትተኛ ታውክሃለች። ሁለተኛውና ከዚያ የሚከፋው ደግሞ በመንደፍ ደምን መምጠጧና በሽታ ማምጣቷ ነው። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዓውድ ውስጥም ከፍተኛ ድምፅ በማሰማት ለማወክ የሚሞክሩ፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማደናቀፍና ህልውናዋን ለመገዳደር ከሚፈልጉ ኃይሎች ጋር እስከመሰለፍ የሄዱ አካላት ነበሩ።»
በወቅቱ በተፈጠሩት ነገሮች ምክንያት በሕዝቡ ዘንድ ምንድን ነው የመጣብን ሥጋት ተፈጥሮ የነበረ ቢሆንም፣ ነገሮች እያዋሉ እያደሩ ሲመጡ ግን የ«መደመር» መንገድ ብቸኛው አማራጭ መሆኑንና ለመበልጸግ የሚደረገው ጥረት ተገቢ መሆኑን ሕዝቡ ማመኑን ገልጸዋል።
በመጨረሻም፣ ሕዝቡ ይህንን እምነቱን በምርጫ ማረጋገጡን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ብቸኛው ኢትዮጵያን የማጽኛ መንገድ ታሪካዊውን ውህደትና እህትነት በሚያርቅ፣ በሚያድስና በሚያሰፋ መንገድ መሄድ፣ ተከባብሮና ተዋዶ በጋራ በመስራት ሀገርን ማጽናት ብቻ መሆኑን አብራርተዋል።
@Seledadotio
@Seledadotio

Source: SeledaPost

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1