በ24 ሰዓታት ጊዜ 60 ሺህ ጥገኝነት ፈላጊዎች ባህሩን ዋኝተው በማቋረጥ ሴኡታ መግባታቸውን የደሴቲቱ ሹሞች እንደተናገሩ አልጀዚራ ፅፏል፡፡
የሞሮኮ ድንበር ጠባቂዎች ፍልሰተኞቹ ወደ ሴኡታ እንዳይገቡ በመከላከል ላይ ናቸው ተብሏል፡፡
ስፔን ከአቅም በላይ የሆነውን የስደተኞች ጎርፍ ለመከላከል ወደ ሴኡታ ተጨማሪ ወታደሮችን መላኳ ታውቋል፡፡
በዚሁ ቀውስ ምክንያት የስፔኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ ትናንት በሴኡታ ጉብኝት ማድረጋቸው ተሰምቷል፡፡
በአውሮፓ የሚገኙ ቀኝ አክራሪ የፖለቲካ ማህበራት የፔድሮ ሳንቼዝ መንግስት ስደተኞችን በተመለከተ ይከተለዋል ያሉትን ለዘብተኛ አቋም አጥብቀው እየነቀፉ ነው ተብሏል፡፡
ስፔን ቀደም ሲል ወደ አገሪቱ ከገቡ ሰነድ አልባ ስደተኞች ለ500 ሺህ ያህሉ ቋሚ የመኖሪያ እና የስራ ፈቃድ ለመስጠት በሂደት ላይ እንደሆነች መረጃው አስታውሷል፡፡
የፍልስጤማውያን የጦር እና የፖለቲካ ድርጅት /ሐማስ/ በሙሉ ትጥቅ ለመፍታት ተስማምቷል ቢባልም አሁንም የጉዳዩ አወዛጋቢነት ቀጥሏል ተባለ፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሐማስን ትጥቅ መፍታት ተከትሎ የእስራኤል ጦር ከጋዛ እንደሚወጣ መናገራቸውን ቢቢሲ ፅፏል፡፡
አንድ የእስራኤል ሹም ጦራችን ከጋዛ የሚወጣው ሐማስ ሙሉ በሙሉ ትጥቅ ከፈታ በኋላ ነው ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
ሐማስ በበኩሉ ከባባድ የጦር መሳሪያዎቼን የማስረክበው የእስራኤል ጦር ሙሉ በሙሉ ከጋዛ ሲወጣ ነው በማለት ላይ ይገኛል፡፡
የፍልስጤማውያኑ የጦር እና የፖለቲካ ድርጅት ትጥቅ ለመፍታት ተስማምቷል ቢባልም በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው ስር የሰደደ ያለመተማመን በሂደቱ ላይ እንቅፋት እንደሚፈጥር ተገምቷል፡፡
የእስራኤል ጦር በአሁኑ ወቅት የጋዛ ሰርጥን 70 በመቶ ክፍል ተቆጣጥሮ ይገኛል፡፡
አሜሪካ እና ኢራን በጦር መዛዛታቸውን እንደቀጠሉ ነው፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራንን በከባዱ እንደበድባታለን ብለው መዛታቸውን አልጀዚራ ፅፏል፡፡
አብዮታዊ ዘብ የተሰኘው የኢራን የጦር ክፍልም እኛም ለምላሹ ዝግጁ ነን ማለቱ ተሰምቷል፡፡
የኢራን ጦር ትናንት በኩዌት የሚገኘውን የአሜሪካ የአህመድ አል ጃቤር የአየር ሀይል ሰፈርን ዒላማ ያደረገ ጥቃት ፈፅሜያለሁ ማለቱ ተሰምቷል፡፡
በዚያ የአውሮፕላኖች መጠለያዎች እና የሳታላይት ግንኙነት አውታሮችን መምታቱ ተጠቅሷል፡፡
በኦማን የባህር ክፍል አንድ የጭነት መርከብ ለጊዜው ምንነቱ ባልተለየ ተተኳሽ መመታቱ ታውቋል፡፡
በመርከቡ የሞተር ክፍል ላይ ጉዳት መድረሱ ቢነገርም ባህረኞቹ ክፉ እንዳልገጠማቸው ተጠቅሷል፡፡
በፓኪስታን በአንድ የድንጋይ ከሰል ማውጫ የማዕድን ስፍራ የደረሰ ፍንዳታ በጥቂቱ 34 ሰዎችን ገደለ ተባለ፡፡
የማዕድን ስፍራ ፍንዳታው ያጋጠመው ባሉቺስታን በተባለችዋ ግዛት እንደሆነ AFP ጽፏል፡፡
በአደጋው መሞታቸው ከተረጋገጠው ሌላ በርካቶች ደግሞ በጉድጓድ ውስጥ ተቀብረው እጣ ፍንታቸው አልለየለትም ተብሏል፡፡
ታላቅ የነፍስ አድን ጥረት እየተደረገ መሆኑ ታውቋል፡፡
የማዕድን ስፍራው ፍንዳታ በምን ምክንያት እንዳጋጠመ ለጊዜው የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡
ከነፍስ አድኑ ጥረት በተጓዳኝ የአደጋ ምርመራ እየተደረገ ነው ተብሏል፡፡
በፓኪስታኗ ባሉቺስታን ግዛት መሰል የማዕድን ስፍራ የስራ ላይ አደጋ እንደሚደጋገም መረጃው አስታውሷል፡፡
የኔነህ ከበደ
Source: Yeneta Tube









No comments yet.