ከፍትፍቱ ፊቱ ይላል የሀገሬ ሰው

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | ​ቱሪዝም እጅግ በከፍተኛ ጥንቃቄ የሚከወን ረብጣ ቢሊየን ገንዘቦች የሚያንቀሳቅስ ዘርፍ ነው።

ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ ”የመደመር መንግስት” በተሰኘው መጽሐፋቸው ቱሪዝም የመንግስታቸው ዋና የኢኮኖሚ ምሰሶ መሆኑን ገልጠዋል።

ለዚህም ማሳያ ይሆን ዘንድ ከግራም ከቀኝም የተሰሩ እና እየተሰሩ ያሉ የቱሪስት መዳረሻ ማዕከላትን መመልከት በቂ ይሆናል።

”ከፍትፍቱ ፊቱ” እንዲል የሀገሬ ሰው ፤ እንግዶች ከአየር መንገድ ተነስተው ወደ ሁሉም መዳረሻዎች እስኪደርሱ ድረስ ከደረሱም በኋላ በሚያገኙት አገልግሎት ለስራ የተመደቡት ግለሰቦች ያለሆነ ፊት እንኳን ካሳዩ ቱሪስቶቹን ማስደንበራቸው አይቀርም።

በዚህ ዘመን ሰውን የመንከባከብ ነገር ሳይንስ ሆኗል።ሳይንስ ደግሞ በስርዓተ ትምህርት ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ አንዳች ለውጥ ለማምጣት ሰዎችን በማሰልጠን መርህ ማድረግ ይቻላል።

የሀገሩን ቱሪዝም ስልጠና የሚመራው የፌደራል ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በሆሳዕና ከተማ 2018 ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ፣ የበጎ አድራጎትና ማህበረሰብ አገልግሎት ማስጀመሪያ ዝግጅት እየተከናወነ ነው።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ ተቋሙ ስልጠናን በላቀ ደረጃ በመስጠት የሀገሪቱን የቱሪዝም መስተንግዶ ጥራት ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር እየሰራ ነው ብለዋል።

​ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ከመደበኛው የስልጠና ማዕቀፍ ባለፍ በአገልግሎት ሰጪ ግለሰቦች የግንዛቤ ስልጠናዎች እየተሰጣቸው ነው።

በዚህም መሰረት በሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች፣ እንዲሁም የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች (በተለይም የሜትር ታክሲ አሽከርካሪዎች) የደንበኛ አያያዝ እና መስተንግዶ ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ተደርጓል።

ከዚህም በተጨማሪ ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁ ስራ አጥ ወጣቶች በዘርፉ የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው ታስቦ በርካታ ስራዎች በመሠራት ላይ ናቸው።

በተጨማሪም ​ኢትዮጵያ በቅርቡ እንድታዘጋጅ የተመረጠችውን ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP 32) ተከትሎ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው እንግዶች ወደ ሀገር እንደሚገቡ ይጠበቃል።

ይህንን ታሳቢ በማድረግ ከአየር መንገድ አቀባበል ጀምሮ እስከ ሆቴል መስተንግዶ ድረስ ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ማሳደግ የዚህ ዓመት ትልቁ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አቶ ጌታቸው አብራርተዋል።

እንግዶች ወደ ሀገር ሲገቡ አየር መንገድ ላይ ከሚያገኙት የመጀመሪያ አቀባበል አንስቶ የሚስተናገዱበት ሁኔታ ሀገርን የሚወክል በመሆኑ በዚህ ዙሪያ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ይሰጣል።

ኢትዮጵያ ከአፍ የወደቀ ጥሬ ዋርካ የሚሆንባት ምድር ናት።ፈጣሪ ሁሉን ሰጥቶን ሲያበቃ ፀጋዎቻችንን ካክፋፋን ልክ አይሆንም።

​ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢንስቲትዩቱ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻ በሆኑት እንደ ጎርጎራ፣ ወንጪ፣ ሀላላ ኬላ እና ጨበራ ጩርጩራ ባሉ አካባቢዎችም የዳሰሳ ጥናቶችን በማካሄድ በአካባቢው ላሉ ነዋሪዎች ጭምር የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎች እየተሰሩ ነው።

አቶ ጌታቸው ማህበረሰቡ ሀገሩን በማስተዋወቅ ረገድ የራሱን አምባሳደራዊ ሚና እንዲወጣና የእንግዳ ተቀባይነት ባህሉን ይበልጥ በማሳደግ ለታላቁ ነገር እንዲዘጋጅ ከአደራ ጭምር አሳስበዋል።

ለ Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን) ሚዲያና ኮሙኒኬሽን

ያፌት ገ/ህይወት

ከሀዲያ ዞን ፤ ሆሳዕና


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: