ከኢትዮጵያ እና አለምአቀፍ ህጎች ማእቀፍ አንጻር
መግቢያ
#Ethiopia | በወንጀል፣በፍትሃብሔር ፣ በዲስፕሊን፣ አስተዳደር ጉዳዮች እንዲሁም ሌሎች ይግባኝ እና የመሳሰሉት ቅሬታዎች ተከሳሾች ላይ ሲቀርብ በግልጽ በህጎች ላይ የተቀመጡትን የመጥርያ ስነስረአቶች አቀራረብ እና አደራረስ የህገመንግስት ፣ አጠቃላይ አለም አቀፍ ፣ የህግ መርሆች እና ስነስረአቶች በጥልቅ በመረዳት ለተከሳሾች ከበቂ እና ምክንያታዊ ጊዜ ጋር በማገናዘብ ሊደርሰው ያስፈልጋል።
ይህ የዜጎችን ህገመንግስታዊ ፍትህ የማግኘት መብት አንቀጽ 37 ን ተፈጻሚ ከማድረግና በህዝብ መካከል ያለውን የፍትህ ሚዛናዊነት የሚያስጠብቅ ነው። ይህንን የክስ ፣ አቤቱታ፣ቅሬታዎችን ተቀብሎ ፍትሀዊ ሚዛን ፣ ፍርድ ፣ ወይም ውሳኔ ከማስጠበቅ አንጻር ጉልህ ሚና ያላቸው እንደመሆናቸው መጠን እነዚህ አቤቱታዎች የቀረቡባቸው የፍትህ ተቋማት ፣ አስተዳደራዊ የቅሬታ ሰሚ እና ውሳኔ ሰጪ ተቋማት ይህንን ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ከሚገባቸውም በላይ ኃላፊነት ያለባቸው እንደመሆናቸው መጠን ባያድርጉ የዚህን ስነስረአት እና ጉድለት ያስከተለ ወገን ከተጠያቀነት ባለፈ በማህበረሰቡ ዘንድ መተማመን የሚያሳጣ እና ለፍትህ ስረአቱ ያላቸው ታማኝነትን የሚያጎድል መሆኑን ማሳያ ነው። በዚህ ጹሁፍ የተከሳሾችን መልስ የማቅረብ ፣የመከላከል እና የመከራከር መብትና ውጤቶች ከህግ አንጻር እንመለከታለን።
1. ስለ ተከሳሾች መልስ የማቅረብና የመከራከር መብት ከኢፊድሪ ህገመንግስት አንጻር
ስለ ተከሳሾች መብት ህገመንግስታችን በምእራፍ ሶስት ላይ በደንብ ዘርዝሮ መልስ እንዲያቀርቡ እና የመከራከር መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ይህም በግልጽ ችሎት በሚገባቸው ቋንቋ ጠበቃም ከሌላቸው መንግስት መድቦላቸው እንዲከራከርላቸው ይደነግጋል።
ይህ ፍትሀዊ ፣ እውነትነት ፣ ተጨባጭ ፣ ሚዛናዊ ፍርድ እንዲሰጥ ዜጎች በህገመንግስቱ አንቀጽ 25 ላይ የተቀመጠውን የእኩልነት መብት ተፈጻሚ ለማድረግ የሀገሪቱን የፍትህ ስረአት ተአማኒነት ኖሮት ዜጎች በህጉ ተማምነው በሰላም እንዲኖሩ ለማድረግ ነው። ከዚህ አንጻር የኢፊድሪ ህገመንግስት አንቀጽ 19 እና 20ን ድንጋጌዎችን ያስቀመጥን ሲሆን አንቀጽ 19 ስለ ተያዙ የወንጀል ተጠርጣሪዎች መልስ የመስጠትና የመከራከር መብቶችን የሚደነግግና የሚያብራራ ሲሆን አንቀጽ 20 ደግም ስለተከሰሱ ሰወች አጠቃላይ መልስ የመስጠትና የመከራከር መብቶች በጥብቅ ሊታይ እንደሚገባ የህገመንግስታዊ መብቶችን ያስቀምጣል።
ይህ የተጣሰ እንደሆነ የጣሰው አካል ህገመንግስታዊ ጥሰት ፈጽሟል የሚያስብል ሲሆን ይህ ይህ የህገመንግስቱን ተፈጻሚነት አደጋ ላይ የሚጠል ሰው ወይም ኃላፊ ነው ለማለት የሚቻል ሲሆን ከዚህም ባለፈ የዜጎችን ፣ የሰወችን ወይም ህጋዊ ሰውነት የተሰጣቸውን አካላት የተከሰሱ ሰወች ህገመንግስታዊ መብት አደጋ ላይ የሚጥል ነው ማለት ነው። ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ የህገመንግስቱን የተከሳሾን መብት ከዚህ ጹሁፍ መልእክት አንጻር አስቀምጫለው።
አንቀጽ 19 የተያዙ ሰዎች መብት
19.1. ወንጀል ፈጽመዋል በመባል የተያዙ ሰዎች የቀረበባቸው ክስና ምክንያቶቹ በዝርዝር ወዲያውኑ በሚገባቸው ቋንቋ እንዲነገራቸው መብት አላቸው፡፡
19.2. የተያዙ ሰዎች ላለመናገር መብት አላቸው፤ የሚሰጡት ማንኛውም ቃል ፍርድ ቤት በማስረጃነት ሊቀርብባቸው እንደሚችል መረዳት በሚችሉት ቋንቋ እንደተያዙ ወዲያውኑ ማስገንዘቢያ እንዲሰጣቸው መብት አላቸው፡፡
19.3. የተያዙ ሰዎች በአርባ ስምንት ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት የመቅረብ መብት አላቸው፡፡ ይህም ጊዜ ሰዎቹ ከተያዙበት ቦታ ወደ ፍርድ ቤት ለመምጣት አግባብ ባለው ግምት የሚጠይቀውን ጊዜ አይጨምርም፡፡ ወዲያውኑ ፍርድ ቤት እንደቀረቡ በተጠረጠሩበት ወንጀል ለመታሰር የሚያበቃ ምክንያት ያለ መሆኑ ተለይቶ አንዲገለጽላቸው መብት አላቸው፡፡
19.4. የያዛቸው የፖሊስ መኮንን ወይም የሕግ አስከባሪ በጊዜው ገደብ ፍርድ ቤት በማቅረብ የተያዙበትን ምክንያት ካላስረዳ፣ ፍርድ ቤቱ የአካል ነጻነታቸውን እንዲያስከብርላቸው የመጠየቅ ሊጣስ የማይችል መብት አላቸው፡፡ ሆኖም ፍትሕእንዳይጓደል ሁኔታው የሚጠይቅ ከሆነ ፍርድ ፡፡
አንቀጽ 20
የተከሰሱ ሰዎች መብት
20.1. የተከሰሱ ሰዎች ክስ ከቀረበባቸው በኃላ ተገቢ በሆነ አጭር ጊዜ ውስጥ በመደበኛ ፍርድ ቤት ለሕዝብ ግልጽ በሆነ ችሎት የመሰማት መብት አላቸው፡፡ ሆኖም የተከራካሪዎቹን የግል ሕይወት፣ የሕዝብን የሞራል ሁኔታና የሀገሪቱን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል ብቻ ክርክሩ በዝግ ችሎት ሊሰማ ይችላል፡፡
20.2. ክሱ በቂ በሆነ ዝርዝር እንዲነገራቸው እና ክሱን በጽሁፍ የማግኘት መብት አላቸው፡፡
20.3. በፍርድ ሂደት ባሉበት ጊዜ በተከሰሱበት ወንጀል እንደ ጥፋተኛ ያለመቆጠር፣በምስክርነት እንዲቀርቡም ያለመገደድ መብት አላቸው፡፡
20.4. የቀረበባቸውን ማናቸውንም ማስረጃ የመመልከት፣ የቀረቡባቸውን ምስክሮች የመጠየቅ፣ ለመከላከል የሚያስችላቸውን ማስረጃ የማቅረብ ወይም የማስቀረብ እንዲሁም ምስክሮቻቸው ቀርበው እንዲሰሙላቸው የመጠየቅ መብት አላቸው፡፡
20.5. በመረጡት የሕግ ጠበቃ የመወከል ወይም ጠበቃ ለማቆም አቅም በማጣታቸው ፍትሕ ሊጓደል የሚችልበት ሁኔታ ሲያጋጥም ከመንግሥት ጠበቃ የማግኘት መብት አላቸው፡፡
20.6. ክርክሩ በሚታይበት ፍርድ ቤት በተሰጠባቸው ትእዛዝ ወይም ፍርድ ላይ ሥልጣን ላለው ፍርድ ቤት ይግባኝ የማቅረብ መብት አላቸው፡፡
20.7. የፍርዱ ሂደት በማይገባቸው ቋንቋ በሚካሄድበት ሁኔታ በመንግሥት ወጪ ክርክሩ እንዲተረጐምላቸው የመጠየቅ መብት አላቸው፡፡
2. የተከሳሾች መልስ የመስጠት እና የመከራከር መብት ከአለምአቀፍ ስምምነቶች አንጻር
የተከሰሱ ሰዎች ክስ በቀረበበት ጊዜ በቂ መረጃ አግኝተው መልስ የመስጠት እና በማስረጃ የመከላከል መብት አላቸው። ይህ መብት የዓለም አቀፉ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን (ICCPR) አንቀጽ 14 ላይ የተደነገገ ሲሆን የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 20 ላይም ቀደም ሲል በገለጽነው ላይ የተቀመጠ በመሆኑ ዓለም አቀፍና ሐገራዊ ሕጎች የተረጋገጠ መሠረታዊ የፍትህ መርህ ነው። የዓለም አቀፍ ስምምነቶች ተከሳሾች መልስ የመስጠትና የመከላከል መብቶቻቸውን አስመልክቶ ክስን በቂ በሆነ ዝርዝር ማወቅ ፣ ተከሳሹ በቀረበበት ወንጀል ዙሪያ በዝርዝር እና በሚገባው ቋንቋ የክሱን ይዘት በጽሑፍ የማግኘት መብት ፣ የመሰማት እና መልስ የማቅረብ መብት ፣ ፍርድ ቤት ቀርቦ በራሱ ወይም በምርጫው ጠበቃ አማካኝነት ክሱን ተረድቶ የመልስ ምላሽ የመስጠት መብት እንዳለው ፣ ማስረጃን የመከላከል እና የመከራከር መብት ፣ በቀረቡበት ምስክሮች ላይ ጥያቄ የማቅረብ፣ የራሱን መከላከያ ማስረጃዎች የማቅረብ እና የማስቀረብ መብት ፣ ከወንጀል ነፃ ሆኖ የመቆጠር መብት ፣ ጥፋተኛነቱ በሕግ እና በማስረጃ እስከሚረጋገጥ ድረስ ማንኛውም ተከሳሽ ንጹህ ሆኖ እንደሚቆጠርና ይህም በህገመንግስታችን የተቀመጠ ሲሆን ሀገራችን የህጋችን አካል አድርጋ በኢፊድሪ ህገመንግስት አንቀጽ 13 መሠረት አጽድቃለች። ይህ ከሆነ መንግስት በህገመንግስታችን አንቀጽ 9/1/ መሠረት የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ረገድ ተገቢውን የህግ የበላይነት ማስከበር የሚገባው ሲሆን ከዚህ መሠረታዊ የተከሳሽ መብቶች መርህን ባፈነገጠ መንገድ የሚያስኬድ ማንኛውም አካል ላይ ይግባኝ ወይም አስተዳደራዊ ቅሬታዎችን በማቅረብ ሊታረም እንደሚችል በህገመንግስቱና በሌሎች ህጎች ተቀምጧል።
3. የፍትሀብሔር ስነስረአት ህግ አላማ ፣ የተከሳሾች መልስ የማቅረብ እና የባለጉዳዮች ቀርቦ መከራከር መብት መከራከር
3.2 የፍ/ስ/ስ/ህግ ቁጥር ከ65_78 የተከራካሪዎች መቅረብ መብት ከተከሳሾች መብት አንጻር
በእነዚህ ድንጋጌዎች ውስጥ ተከራካሪዎች በእኩልነት አቤቱታዎችን አቅርበው ተከሳሽም ክስ መጥሪያ ደርሶት መልስ አቅርቦ የመከራከር ፣ የመልስ ዝርዝሩን የማሰማት መብት እንዳለው ይደነግጋል።ከሳሽ በመጀመሪያው የክስ መስማት ቀነ ቀጠሮ ካልቀረበ እንኳን ተከሳሽ ቀርቦ በፍትሃብሔር ስነስርአት ህግ ቁጥር 73 እንኳን መዝገቡ የሚዘጋ ሲሆን ይህ የተከሳሽን መብት የሚሰጥ ነው።
በዚህ በመጀመሪያ ክስ መስማት ቀነ ቀጠሮ ሁለቱም ካልቀረቡ በፍትሃብሔር ስነስርአት ህግ ቁጥር
69 መሠረት መዝገቡ የሚዘጋ ሲሆን ይህም የተከሳሽ መብትን ሊያስጠብቅ የሚችል ከሳሽ ባልፈለገበት ወይም ዳተኝነት ባሳየበት ተከሳሽ ስለተከሰሰ ብቻ ክሱ የማይቀጥል መሆኑን ያሳያል።
ሌላው እነዚህ ድንጋጌዎች ውስጥ በጥልቅ የተከሳሽን መልስ የመስጠትና የመከራከር መብቶችን በጉልህ የሚያስረዳ በጥልቅ የሚተነትን ድንጋጌዎች ሲሆኑ በፍትሃብሔር ስነስርአት ህግ ቁጥር 78ን ለማሳያ ያህል ስናነሳ ተከሳሽ በሌለበት የተሰጠ ትእዛዝ፣ብይን፣ውሳኔ ቢኖር እንኳን የተከሳሽን መልስ የመስጠት እና በፍርድ ቤቱ በመገኘት የመከራከሩን መብት ለማስጠበቅ ተከሳሽ በሌለበት የተሰጠው ውሳኔ ተነስቶ ባለበት መልስ የማቅረብ እና የመከራከሩን መብት ለማስጠበቅ የሚችል ድንጋጌ ነው። እነዚህ አጠቃላይ ድንጋጌዎች የተከሳሽን መብቶች ፍትሀዊ ውሳኔዎች ለማሰጠት የሚያስችሉ ድንጋጌዎች ናቸው።
4. በፍትሃብሔር ስነስርዓት ህግ ድንጋጌዎች ቁጥር ከ94-110 ደረስ የተከሳሽ መጥሪያ አደራረስ ስነስርዓት
እነዚህ ድንጋጌዎች ለተከሳሽ ክስ እና መጥርያ በአግባቡ መድረስ እንዳለበት በተለያየ የመጥርያ ስነስረአት ደንብ መሠረት
አማራጮችን በማስቀመጥ ጭምር በጥብቅ የተከሳሽን መልስ አቀራረብና መከራከር መብት አንጻር በከፍተኛ ትጋትና ህገመንግስታዊ መብቶች ጥበቃ መሠረት አድርጎ የሚያስጠብቅ ሲሆን ይህንንን ስነስረአት በጣሰ መልኩ የሚፈጸሙ አካሄዶች የተከሳሽን መብት የሚጋፋ በመሆኑ ተከሳሽ በሌለበት የሚሰጡ ትእዛዝ ፣ ብይን፣ውሳኔ ፍርዶች ላይ ተከሳሽ ባወቀ ጊዜ በማሰረዝ
ባለበት የክስ መስማት ሂደቱ ሊቀጥል እንደሚችል በፍትሃብሔር ስነስርዓት ህግ ቁጥር 78 ላይ ተደንግጎ ተቀምጧል።
እነዚህን ከላይ ያነሳናቸውን ከፍተሀብሔር ስነስረአት ህግ ድንጋጌዎች አላማ አንጻር በጥቂቱ ለምሳሌ ያህል አነሳን እንጂ በክርክር፣ክስ በመስማት፣በመስማት ፣ በሙግት፣በትእዛዞች አሰጣት፣አስተያየት ፣ምስክር አሰማም፣ፍርድ ማንበብ ፣ በግልጽ ችሎት የመሰማት መብት ፣ ተጨማሪ ማስረጃዎች አቀራረብ፣አፈጻጸም አንጻር የተከሳሾችን ያለአድልዎ በእኩልነት ከመዳኘት አንጻር የተከሳሾችን መብት መጠበቅ በጥብቅ ከግንዛቤ የሚያስገባ ነው።
5. የኢትዮጵያ ወንጀል ስነስርዓቶች ከተከሳሽ መልስ የማቅረብና የመከላከል መብት አንጻር
የተከሳሽ መልስ የመስጠትና የመከራከር መብት በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት እና በወንጀል ሕግ ሥነ ሥርዓት መሠረት ተከሳሹ የቀረበበትን ክስ የመረዳት፣ ክሱን የመቃወም ወይም የመካድ፣ የማስረጃ ዝርዝር የማወቅ እና ራሱን በነጻነት የመከላከል ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና ያለው መሠረታዊ ሰብአዊ መብት ነው።የክስ ንባብና መልስ አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓትክስ የማወቅ መብት ተከሳሽ ያለው በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ ሲቀርብ የክሱን ይዘትና ዝርዝር ያነብበለታል፤ እንዲሁም ያስረዳዋል።
ክሱ ከተነበበ በኋላ ተከሳሹ በክሱ ላይ እውነት መሆኑን ወይም አለመሆኑን (እንዲሁም ጥፋተኛ መሆን አለመሆኑን) እንዲያምን ወይም ምላሽ እንዲሰጥ ይጠየቃል። በመቀጠልም ተከሳሹ ወንጀሉን ከፈጸመ ዕምነት ሊሰጥ (ሊቀበል) ይችላል፤ ወንጀሉን ካካደ ደግሞ ክህደት ቃል በመስጠት ከሳሽ አካል (አቃቤ ሕግ) ማስረጃውን እንዲያሰማ ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ሊሰጥ እንደሚችል ይደነግጋል።
ፍርድ ቤቱም ተከሳሹ ሲቀርብ የክሱን ይዘትና ዝርዝር ያነብበለታል፤ እንዲሁም ያስረዳዋል። ክሱ ከተነበበ በኋላ ተከሳሹ በክሱ ላይ እውነት መሆኑን ወይም አለመሆኑን (እንዲሁም ጥፋተኛ መሆን አለመሆኑን) እንዲያምን ወይም ምላሽ እንዲሰጥ ይጠየቃል። ተከሳሹ ወንጀሉን ከፈጸመ ዕምነት ሊሰጥ (ሊቀበል) ይችላል፤ ወንጀሉን ከካደ ደግሞ ክህደት ቃል በመስጠት ከሳሽ አካል (አቃቤ ሕግ) ማስረጃውን እንዲያሰማ ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ይሰጣል።የተከሳሽ የመከራከርና የመከላከል መብቶችማስረጃን የመጠየቅና የመቃወም መብት አስመልክቶም ተከሳሹ በአቃቤ ሕግ የቀረቡበትን የሰነድም ሆነ የሰው ምስክሮች የመጠየቅና የመፈተሽ መብት አለው።
የመከላከያ ምስክር ማሰማት አስመልክቶም አቃቤ ሕግ ማስረጃውን ከዘጋ በኋላ ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ ራሱን ለመከላከል የሚያስችለውን የሰው ወይም የሰነድ ማስረጃ ማቅረብ እንደሚችል ይነግረዋል። ከዚህም በኋላ ተከሳሹ በሕግ ባለሙያ (በጠበቃ) ታግዞ የመከራከር፣ አቅም ከሌለውም የመንግስት ጠበቃ እንዲመደብለት የመጠየቅ መብት ያለው ሲሆን ክሱ እስከሚጠናቀቅበትና የማጠቃለያ ሀሳብ እስከሚሰጥበት ጊዜ ድረስ ተከሳሹ የመסማት እና የመከራከር ሙሉ ዕድል እንዳለው የቀድሞውም ሆነ የአሁኑ የወንጀል ስነስረአት ህግ ድንጋጌዎች እንዲሁም ሌሎች አግባብነት ያላቸው የወንጀል ስነስረአት ህጎች ያስቀምጣሉ።
6. የዲስፕሊን እና ሌሎች የአስተዳደር ክሶች ፣ ቅሬታዎች እና አቤቱታዎች
ከላይ አጠቃላይ የተመለከትናቸው አጠቃላይ የተከሳሽ መልስ የማቅረብ እና በእኩልነትና የመከራከር መብቶች አለምአቀፋዊ እና ህገመንግስታዊ መብቶች እንደመሆናቸው መጠን ይህንን ተፈጻሚ ከማድረግ አንጻር ማንኛውም የቅሬታ ሰሚ አስተዳደር አካላት ተፈጻሚ ከማድረግ አንጻር ግዴታቸውን ሊወጡ ያስፈልጋል።
የኢፊድሪ ወንጀል ህግ አጠቃላይ የወንጀል ህግ መርሆችንም እንደሚያስቀምጠው የዲስፕሊን ክስ አቤቱታዎችም እነዚህን የወንጀል ህጉን መርሆች ሊከተሉ እንደሚገባ እና የየህግመንግስቱ አንቀጽ 20ም አንጻር ተግባራዊ ሊሆን የሚገባ ሲሆን ይህን በጣሰ መልኩ በማስኬድ የተከሳሸን መልስ የማቅረብ እና የመከራከር መብትን አለመጠበቅ የተከሳሹን በኢፊድሪ ህገመንግስት አንቀጽ 37 ላይ የተቀመጠውን ፍትህ የማግኘት መብት የሚሸረሽር ነው።
7. የተከሳሽ መልስ የማቅረብና የመከራከር መብት ከፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አስገዳጅ የህግ ትርጉም አንጻር
7.1 በፍትሃብሔር ጉዳዮች
የተከሳሽ መልስ የማቅረብና የመከራከር መብት ሕገ-መንግሥታዊ እና መሠረታዊ የዳኝነት ዋስትና ነው። የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ተከሳሽ/ተጠሪ መልስና መከላከያ እንዳያቀርብ መብቱ ታልፎ ወይም ተከልክሎ የሚሰጥ ውሣኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት መሆኑን በመዝገብ ቁጥር 158462 እና መዝገብ ቁጥር 69302 ላይ በአስገዳጅነት አረጋግጧል።
ሕጋዊ መርሆዎችና የሰበር ትርጉምየመሰማት መብት (Right to be Heard) ላይ ማንኛውም ተከሳሽ ወይም ተጠሪ በቀረበበት ክስ ላይ የጽሁፍም ሆነ የቃል መልስ እንዲሁም መቃወሚያዎችን የማቅረብ ሕጋዊ መብት ያለው ሲሆን የሥር ፍርድ ቤቶች ተከሳሽ መልስ ሳይሰጥ ወይም መብቱ ታልፎ ውሣኔ መስጠታቸው መሠረታዊ የሕግ ስህተት እንደሆነ ሰበር ሰሚ ችሎቱ አስገዳጅ ትርጉም ሰጥቷል።የመቃወሚያ አቀራረብ በተመለከተም ተከሳሽ በጽሁፍ መልስ ባያቀርብም እንኳ በቀጠሮ ቀን ወይም በቃል ክርክር ወቅት እንደ ይርጋ ያሉ መሠረታዊ መቃወሚያዎችን የማንሳት መብቱ ሊጠበቅለት እንደሚገባ ተገልጿል።
7.2 በወንጀል ጉዳዮች
በወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓት ሂደት ውስጥ የተከሳሽ መልስ የማቅረብ፣ የመሰማት እና የመከራከር መብት መሠረታዊ የሕገ-መንግሥት (አንቀጽ 20) እና የተፈጥሮ ፍትህ (Natural Justice) መርህ ነው። የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በዚህ መብት ዙሪያ በርካታ አስገዳጅ የሕግ ትርጉሞችን የሰጠ ሲሆን፥ በወንጀል ጉዳይ በመዝገብ ቁጥሮች እና መርሆች ላይ ውሳኔ ሰጥቷል።. የሰበር መዝገብ ቁጥር፦ 73387 አስገዳጅ የሕግ ትርጉም፦ አንድ ተከሳሽ የቀረበበትን የላላ ወይም ግልጽ ያልሆነ የጽሑፍ ክስ በዝርዝር የመረዳት እና መቃወሚያ የማቅረብ መብት አለው።
ፍርድ ቤት ተከሳሹ የቀረበበትን ክስ ሳይረዳ ወይም መቃወሚያ የማቅረብ መብቱን ሳይጠቀምበት በቀጥታ ወደ ጥፋተኝነት ውሳኔ መሻገር የለበትም።አንድ ተከሳሽ የቀረበበትን የላላ ወይም ግልጽ ያልሆነ የጽሑፍ ክስ በዝርዝር የመረዳት እና መቃወሚያ የማቅረብ መብት አለው። ፍርድ ቤት ተከሳሹ የቀረበበትን ክስ ሳይረዳ ወይም መቃወሚያ የማቅረብ መብቱን ሳይጠቀምበት በቀጥታ ወደ ጥፋተኝነት ውሳኔ መሻገር የለበትም።
ከጥፋተኝነት ውሳኔ በኋላ መልስና አስተያየት የመስጠት መብትየሥነ-ሥርዓት መርህ አስመልክቶ በወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ ቁጥር 149(4) መሠረት ፍርድ ቤቱ የጥፋተኝነት ውሳኔ ከሰጠ በኋላ፥ ዓቃቤ ሕግ ስለ ቅጣት ማክበጃና አስተያየት ከሰጠ በኋላ ተከሳሹ ወይም ጠበቃው የመጨረሻ መልስ የመስጠት እና የቅጣት ማቅለያ የማቅረብ መብት አለው።
ይህንን መብት ሳይሰጡ የሚበየን የቅጣት ውሳኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት እንዳለበት በተደጋጋሚ በሰበር ችሎት ተረጋግጧል።ማጠቃለያ እና ቀጣይ እርምጃ፦በማንኛውም የወንጀል ክርክር ሂደት ላይ ፍርድ ቤቶች ተከሳሽ መልስ እንዲሰጥ እና በማስረጃዎችን እንዲከራከር ዕድል ሳይሰጡ የሚያልፉት ሂደት የሰበር አስገዳጅ ትርጉሞችን የሚጥስ ነው።
8. የጹሁፉ የተከሳሽ መልስ የማቅረብና የመከራከር መብት
ማጠቃለያ
ከላይ በጹሁፉ እንዳስቀመጥነው ተከሳሽ ሲከሰስ በፍትሃብሔር ፣በወንጀልም ሆነ በሌሎች አስተዳደር ጉዳዮች ክስ፣አቤቱታ ወይም ቅሬታ ሲቀርብበት ክስና መጥርያው በቂና በምክንያታዊ ጊዜ ደርሶት መልስ የማቅረብ ቀርቦም የመከራከር መብት እንዳለው በኢፊድሪ ህገመንግስት አንቀጽ 20 ፣ በአለምአቀፍ ህግ ስምምነቶች እና በሌሎች ህጎቻችን የተደነገጉ ሲሆን ከዚህ ውጭ በሚፈጸሙ የስነስረአት ግድፈቶች የተከሳሽን መሠረታዊ መብት የሚጋፋና ዜጎች በህጎች ላይ ያላቸውን እምነት የሚሸረሽርና ዋስትና የሚያሳጣ በመሆኑ ከዚህ አንጻር ግንዛቤ እና እርምት ሊወሰድ የሚገባው መሆኑን ከህገመንግስታችን ጀምሮ በሌሎች ህጎች ተደንግጎዋል።
በህግ ባለሙያ ፋንታሁን ደለለው
https://www.facebook.com/fantahun.delelew.7?mibextid=ZbWKwL
delelewfantahun2010@gmail.com
Source: GetuTemesgen









No comments yet.