በኦቶና ሆስፒታል የላብራቶሪ መሳሪያዎችን ሊሰርቅ የነበረ የጥበቃ ሰራተኛ እጅ ከፍንጂ ተያዘ

- Advertisement -
Sidebar AD

በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል (ኦቶና) ሦስት ወሳኝ የላብራቶሪ ማይክሮስኮፖችን አውጥቶ ለመሰወር ሲሞክር የነበረ የጥበቃ ሰራተኛ በተረኛ ጥበቃዎች ብርቱ ክትትልና ተጋድሎ እጅ ከፍንጂ መያዙ ተገለጸ።

በትላትናው እለተ የተፈጸመው ይህ ድርጊት ተራ የሕክምና ዕቃ ስርቆት ሳይሆን፣ የሺዎችን ሕይወት እና የሆስፒታሉን ዕለታዊ የሕክምና አገልግሎት ቀጥተኛ አደጋ ላይ የጣለ ከባድ ወንጀል መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ተጠርጣሪው ግለሰብ የሕክምና መገልገያዎቹን ደብቆ ከሆስፒታሉ ግቢ ሊያወጣ ሲል በተረኛ ባልደረቦቹ ንቁ ክትትል በቁጥጥር ስር ውሏል። ድርጊቱ በግለሰቡ ብቻ የተፈጸመ ሳይሆን በጀርባ ያሉ አመቻቾችና አቀናባሪዎች እንዳሉበት በመጠረጠሩ፣ ወንጀሉን ያስተባበሩ አካላት በሙሉ ተለይተው ተገቢው የሕግ ትርጉም እንዲሰጣቸውና አስተማሪ ቅጣት እንዲያገኙ ጉዳዩ በትኩረት እየተከታተለ ይገኛል።

በአንድ አጠቃላይ ሆስፒታል ውስጥ ማይክሮስኮፕ ማለት የተደበቁ በሽታዎችን አውጥቶ በማሳየት የሕሙማንን ሕይወት የሚያስጥል ዋና መመርመሪያ መሳሪያ ነው።

እነዚህን መገልገያዎች ማጣት በሕሙማን ላይ የሚከተሉትን ከባድ የጤና አደጋዎች ያስከትላል፦

እንደ ወባ፣ ቲቢ እና የተለያዩ ከባድ የባክቴሪያ ኢንፌክሽኖችን በፍጥነት በመመርመር አስቸኳይ የሕክምና ውሳኔ ለመስጠት ያገለግላሉ።

የደም ማነስን (Anemia) እና የደም ካንሰርን (Leukemia) በጥንቃቄ ለይቶ ለማወቅ ወሳኝ መገልገያዎች ናቸው።

እነዚህ መሳሪያዎች ከአገልግሎት ውጭ ሲሆኑ የላብራቶሪ ውጤቶች ይዘገያሉ፤ ይህም በተለይ በፅኑ ሕሙማን፣ በሕፃናትና ነፍሰ ጡራት ሕይወት ላይ የቀጥታ አደጋ ይደቅናል።

የሕዝብና የመንግሥት ሀብት የሆኑትን የሕክምና መገልገያዎች ከስርቆትና ከእጅ አዙር ሴራ መጠበቅ የሁላችንም ኃላፊነት ነው።

በሆስፒታሉ ግቢ ውስጥ የታየው የተረኛ ጥበቃዎች ንቅናቄ የሚደነቅ ሲሆን፣ የወንጀሉ ተሳታፊዎች በሙሉ ለሕግ እንዲቀርቡ የጀመረው ክትትል ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

Via ጉርሻ page


Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2