ኢራን ከአሜሪካ ጋር እየተነጋገርኩ አይደለም አለች

- Advertisement -
Sidebar AD

ኢራን ሰኞ ዕለት ከአሜሪካ ጋር ምንም ዓይነት ንግግር እያካሄደች አለመሆኗን ገልጻ፣ ከኦማን ጋር በሆርሙዝ ወሽመጥ ደኅንነቱ የተጠበቀ ጉዞ እንዲደረግ የሚያስችል “ጊዜያዊ የባህር መጓጓዣ መስመር” ለመመስረት እየሰራሁ ነው አለች።
የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እስማኤል ባጋይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ቴህራን ከሙስካት ጋር የምታደርገው ንግግር ቁልፍ በሆነው የባሕር መስመር ላይ ጊዜያዊ የመርከቦች መንቀሳቀሻ ለመመስረት ያለመ ነው ብለዋል።

ከኢራን መንግሥት ጋር ቅርበት ያለው ፋርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው ባጋይ “ከኦማን ጋር የምናደርገው የአሁኑ ውይይት በሆርሙዝ ባህር ወሽመጥ ውስጥ የመርከቦችን ደኅንነቱ የተጠበቀ ጉዞ ማረጋገጥ ላይ ያተኮረ ነው” ብለዋል።
“በሆርሙዝ ባህር ወሽመጥ ውስጥ የመርከብ ጉዞ ደኅንነትን ለማረጋገጥ እንዲቻል፣ ከኦማን ጋር በመተባበር በተቻለ ፍጥነት ጊዜያዊ የመተላለፊያ መስመር ለመዘርጋት እየሰራን ነው” ሲሉም አክለዋል።
ባጋይ በቴህራን እና በዋሽንግተን መካከል ንግግር እየተደረገ ነው የሚሉ ዘገባዎችን ውድቅ በማድረግ “ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ድርድር እያደረግን አይደለም” ብለዋል።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር ሰኞ ከሰዓት በኋላ ውይይት እንደሚጀመር ትናንት እሁድ ተናግረው ነበር።

ትራምፕ፣ በሆርሙዝ ጉዳይ እና የኢራንን “ኒውክሌር ማስወገድ” በተመለከተ በቅርቡ ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚቻል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል ።
ባጋይ “አሜሪካ ጥቃቷን እና ክልከላዋን እስከቀጠለች ድረስ [በሆርሙዝ ያለው ሁኔታ ላይ] የሚለወጥ ነገር አይኖርም” ብለዋል።

BBC




Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2