እነሆ ”ተስፋን እንትከል”’

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | ​​​”ዛፍ ለመትከል የተሻለው ጊዜ ከ20 ዓመታት በፊት ነበር፤ ሁለተኛው የተሻለው ጊዜ ደግሞ አሁን ነው” እንደሚባለው ሁሉ፣ ዛፍ መትከል ተስፋን መትከል በመሆኑና ሕይወታችንን ሰናይ ለማድረግ ደኖቻችንን ማልማት አስፈላጊ ነው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የምድራችን 31 ከመቶ የሚሆነው አካል በደን የተሸፈነ ቢሆንም፣ የደን ሽፋን በየጊዜው እያቆለቆለ በመምጣቱ እስከ እ.ኤ.አ 2030 ድረስ 1 ትሪሊዮን ዛፎችን ለመትከልና ለመንከባከብ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል።

በሀገራችን በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ 40 ከመቶ የነበረው የደን ሽፋን ለእርሻ መሬት መስፋፋት ሲባል ተመንጥሮ ወደ 2 ከመቶ ወርዶ የነበረ ቢሆንም፣ ባለፉት አምስት ዓመታት በተደረገው ከፍተኛ ጥረት የደን ሽፋኑ በ2023 ወደ 23.6 ከመቶ ማደግ ችሏል።

በዚህ መነሻም የፌዴራል ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አካል የሆኑ ሀገራዊና ማህበራዊ ልማቶችን አከናውኗል።

በኢንስቲትዩቱ “ተስፋን እንተክላለን” በሚል ሀገራዊ ራዕይ የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በማካሄድ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመተባበር በቦቢቾ ቀበሌ ለምግብነትና ለአካባቢ ጥበቃ የሚውሉ 5 ሺህ ችግኞችን ተክሏል።

ከችግኝ ተከላው ጎን ለጎንም በጀሎ ናረሞ ቀበሌ “የዛሬ ህፃናት የነገ ተስፋ ናቸው” በሚል መሪ ቃል የነገ ሀገር ተረካቢ ህፃናትን አእምሯዊ እድገት ለመደገፍ የሚያስችል ዘመናዊ የመዋዕለ ህፃናት ግንባታ መሠረት ድንጋይ አኖሯል።

​በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ኢንስቲትዩቱ ከግንባታው ባሻገር ለአንድ ሺህ ተማሪዎች የሚሆን የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ለሆሳዕና ከተማ ከንቲባ ለአቶ ሳሙኤል ሽጉጤ እና ለትምህርት ጽሕፈት ቤት ሃላፊው አስረክቧል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሀገራዊ አንድነትን እንደሚያጠናክር ገልጸው፣ ደረጃውን የጠበቀ እና በቴክኖሎጂ የታገዘ የትምህርት ቁሳቁስ የሚሟላለት ይህ መዋዕለ ህፃናት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ ለአገልግሎት እንዲበቃ አስፈላጊው ክትትል እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።

የሆሳዕና ከተማ ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሽጉጤ እና የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች ለተከናወኑት የልማትና የበጎ አድራጎት ሥራዎች ለኢንስቲትዩቱ አመራሮችና ሠራተኞች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ለ Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን) ሚዲያና ኮሙኒኬሽን

ያፌት ገ/ህይወት

ከሀዲያ ዞን ፤ ሆሳዕና






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: