በእንግሊዝ ቻናል በኩል ከፈረንሳይ ወደ ብሪታንያ ለመሻገር ሲሞክሩ የተሳፈሩባት ጀልባቸው በእሳት የተያያዘችባቸውን 173 ስደተኞችን የፈረንሳይና የብሪታንያ ባለሥልጣናት ትናንት ታደጉ። ስደተኞቹን የመታደጉ ዘመቻ ከዛሬ ስምንት ዓመት ወዲህ በዚህ መስመር የተደረገ ትልቁ የሕይወት አድን ዘመቻ ተብሏል።
ስደተኞቹን የጫነችው አነስተኛ ጀልባ በእሳት የተያያዘችው በፈረንሳይና በብሪታንያ የውሀ ክልል ድንበር ላይ ነበር። ጀልባዋ በእሳት ስትያያዝ ስደተኞች ዘለው ለመውጣት ተገደው ነበር ። ይሁንና በአንዳንዶቹ ላይ ከመጠነኛ ቃጠሎ በስተቀር ከባድ ጉዳት አልደረሰባቸውም ተብሏል።
የፈረንሳይ ባህር ኃይል ባለሥልጣናት እንዳሉት ስደተኞቹን የጫነችው ጀልባ የተነሳችው ከፈረንሳይዋ ኖርማዲ የባህር ጠረፍ መንደር ቬልዩ ለሮዝ ነው። ጀልባቸው በእሳት እንደተያያዘች የብሪታንያ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች መርከቦችን እና የሕይወት አድን ጀልባዎችን ትንናት ማለዳ ልከውላቸዋል። ስደተኞቹ ከየትኛዎቹ ሀገራት እንደመጡ ዘገባውን ያወጣው የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት አልጠቀሰም።
የፈረንሳይ የባህር ኃይል ባለሥልጣናት እንደተናገሩት በነዚህ ጀልባዎች ተጭነው ወደ ብሪታንያ የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። ካለፈው ጥር ወዲህ በዚህን መሰል አደገኛ ጉዞ ብሪታንያ የባህር ዳርቻ የደረሱ ሰዎች ቁጥር ከ14, 500 በላይ መሆኑን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
DW Amharic
Source: Yeneta Tube









No comments yet.