#Ethiopia | የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ኢትዮጵያን በ2026 የሚስ ወርልድ ውድድር ለምትወክለው የባህልና ጥበባት አምባሳደር ሞዴል ሩት ይርጋለም የእንኳን ደስ አለሽና የሽኝት መርሃ ግብር አካሂዷል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በመርሃ ግብሩ ላይ ለሞዴሏ መልካም ምኞታቸውን በመግለጽ፣ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረክ በብቃት ወክላ በድል እንድትመለስ ተመኝተዋል።
ሚኒስትሯ ሩት ይርጋለም የባህል አምባሳደር ሆና ከተሾመች በኋላ በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች በመዘዋወር የኢትዮጵያን ብዝሃ ባህላዊ እሴቶች፣ ወጎችና ቅርሶች በቅርበት መረዳቷን ገልጸዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በአማራ ክልል ጎንደር እና በኦሮሚያ ክልል ባሌ ያደረገችው ጉብኝት የአገሪቱን ባህላዊ ሀብት በጥልቀት እንድታውቅ እንዳገዛት ጠቁመዋል።
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፣ ይህ ልምድ ከ130 በላይ አገራት በሚሳተፉበት የሚስ ወርልድ መድረክ ኢትዮጵያን በብቃት ለማስተዋወቅና የአገሪቱን ገጽታ ከፍ ለማድረግ እንደሚያግዛት ተገልጿል።
ሸዊት ሻንካ መላው ኢትዮጵያውያን በውድድሩ ወቅት በሚቀርበው የማኅበራዊ ሚዲያ ድምጽ መስጫ (ሊንክ) አማካኝነት ለሞዴሏ ድጋፍ እንዲያደርጉና ከጎኗ እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።
በበኩሏ ሞዴል ሩት ይርጋለም ለተደረገላት የሽኝትና የመልካም ምኞት መርሃ ግብር ምስጋናዋን ገልጻ፣ ሀገሯን በዓለም አቀፍ መድረክ በክብር ለመወከል ቆርጣ መነሳቷን አረጋግጣለች።
ከውድድሩ በኋላም የኢትዮጵያን ባህላዊና ጥበባዊ እሴቶች ለዓለም ለማስተዋወቅ መሥራቷን ተናግራለች።
በሽኝት መርሃ ግብሩ ላይ የክልልና የከተማ አስተዳደር የባህልና ስፖርት ዘርፍ አመራሮች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የሙያ ማኅበራት አመራሮችና የሞዴሏ ቤተሰቦች በመገኘት ለሩት ይርጋለም የሀገር አደራ ሰጥተዋል።


Source: GetuTemesgen








No comments yet.