4.1 ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት የባሕር ዳር አዲሱ ዓለም አቀፍ ተርሚናል በይፋ ተመረቀ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | የባሕር ዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አዲሱ ተርሚናል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች በተገኙበት በይፋ ተመርቆ ለአገልግሎት ተከፍቷል።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው እንደገለጹት፣ አውሮፕላን ማረፊያው ለበርካታ ዓመታት የማስፋፊያ ሥራዎች ሲከናወኑለት የቆየ ሲሆን፣ በ2013 ዓ.ም በደረሰበት ጉዳት ምክንያት ተርሚናሉን በአዲስ መልክ ለመገንባት በ2014 ዓ.ም ሥራው ተጀምሯል።

አዲሱ ተርሚናል በ8,300 ካሬ ሜትር ስፋት ላይ የተገነባ ሲሆን፣ ዘመናዊ የአየር ማረፊያ መሠረተ ልማቶችን ያሟላ መሆኑ ተገልጿል። በዚህም ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ቀጥሎ በኢትዮጵያ ሁለተኛው ትልቅ የአየር ማረፊያ ተርሚናል ሆኗል።

ተርሚናሉ በአንድ ጊዜ 700 መንገደኞችን ማስተናገድ የሚችል ሲሆን፣ በተመሳሳይ ጊዜ አራት ቦይንግ 777 ወይም ስድስት ቦይንግ 737 አውሮፕላኖችን ማቆም የሚያስችል አቅም አለው።

ለተርሚናሉ ግንባታ 4.1 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉን የገለጹት መስፍን ጣሰው፣ ፕሮጀክቱ የባሕር ዳርን እና የአካባቢውን የቱሪዝም፣ የንግድ እና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በእጅጉ እንደሚያበረታታ ገልጸዋል።

አዲሱ ተርሚናል በኢትዮጵያ የአቪዬሽን ዘርፍ እየተካሄደ ያለውን የመሠረተ ልማት መስፋፋት ከሚያሳዩ ትልልቅ ፕሮጀክቶች አንዱ ሲሆን፣ የአገር ውስጥና የዓለም አቀፍ በረራዎችን በተሻለ ሁኔታ ለማስተናገድ እንደሚያግዝ ይጠበቃል።


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: