ቋሚ ሲኖዶስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጉዳይ የተቋቋመው አጣሪ ኮሚቴ ማስረጃ እንዲቀርብ ጥሪ አቀረበ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ ምርመራ ለማካሄድ የተቋቋመው አጣሪ ኮሚቴ ሕዝብ መረጃና ማስረጃ እንዲያቀርብ ጥሪ አቀረበ።

ኮሚቴው እንደገለጸው፣ በሀገረ ስብከቱና በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ደረጃ የተከሰቱ ሕገ-ወጥ ቅጥር፣ ዕድገትና ዝውውር፣ ሕገ-ወጥ የፋይናንስ አሠራሮችና የገንዘብ ዝውውሮች፣ ሕገ-ወጥ የቦታና የቤት ኪራይ ውሎች፣ ተደራራቢ ሥራዎችና መሰል ጉዳዮችን በዝርዝር በማጣራት ከመፍትሔ ሐሳብ ጋር ሪፖርት ለቋሚ ሲኖዶስ ያቀርባል።

በዚህ ሂደት የማጣራት ሥራው በማስረጃ ላይ የተመሰረተ፣ ተቋም ተኮርና ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጣ እንዲሆን መረጃዎችን መሰብሰብ፣ መተንተን እና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ማደራጀት ዋና የሥራ አቅጣጫው መሆኑን ገልጿል።

ኮሚቴው በተለይም ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በተጠቀሱት እና ተመሳሳይ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ምክንያት ተጎጂ የሆኑ እና በቂ ማስረጃ ያላቸው ግለሰቦች፣ በሥራ ሰዓት የማስረጃቸውን ኮፒ በመያዝ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ በተከፈተው የመረጃ መሰብሰቢያ ቢሮ በመቅረብ፣ በጽሑፍ፣ በድምፅ ወይም በምስል መረጃ እንዲያቀርቡ ጠይቋል።

በተጨማሪም መረጃ የሚያቀርቡ ሰዎች በዚህ ምክንያት ማንኛውም ዓይነት ጉዳት እንዳይደርስባቸው በቋሚ ሲኖዶስ ዋስትና መሰጠቱን አስታውቆ፣ ማንኛውም አካል ያለውን መረጃና ማስረጃ በነጻነት እንዲያቀርብ ጥሪ አቅርቧል።

መግለጫው በአጣሪ ኮሚቴው በሐምሌ 29 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ተሰጥቷል።

Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1

You might want to listen to: