#Ethiopia | በቻይና ሄናን ግዛት የሚኖር አንድ ግለሰብ መጠጥ ጠጥቶ መኪና ሲያሽከረክር ከተያዘ በኋላ ከእስራት ቅጣት ለማምለጥ ሲል የራሱን የሐሰት ሞት እና የቀብር ሥነ-ሥርዓት ከቤተሰቦቹ ጋር በመሆን ማዘጋጀቱ ተገለጠ።
ይህ ግለሰብ ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ ያለ መንጃ ፍቃድ ሲያሽከረክር ተይዞ የተቀጣ ሲሆን በቅርቡ ደግሞ በተመሳሳይ ጥፋት በቁጥጥር ስር ውሎ በዋስ ተለቆ ነበር።
ግለሰቡ የእስራት ቅጣትን በመፍራት የሬሳ ሣጥን በመግዛት በቤቱ ውስጥ ባዶ የመድኃኒት ዕቃዎችን በመበተን እና የሰውነቱን ሙቀት በመቀነስ በከፍተኛ የመድኃኒት መጠን ህይወቱ እንዳለፈ አስመስሎ አዘጋጅቷል።
እናቱ እና አያቱ ፊቱ በከፍተኛ ሁኔታ ስለተበላሸ ማንም ማየት የለበትም በማለት ፊቱን በጨርቅ በመሸፈን ከመሸሹ በፊት በአስቸኳይ የሬሳ ሣጥኑን መሬት ውስጥ እንዲቀበር አድርገዋል።
ተፈላጊው ግለሰብ ወዲያውኑ ወደ ሌላ ግዛት በመኮብለል ሊያመልጥ ችሏል ነው የተባለው።
ፖሊሶች የሞት ዘገባው በደረሳቸው ጊዜ ግለሰቡ ምንም ዓይነት አስቸኳይ የሕክምና እርዳታ አለመፈለጉ እና የሬሳ ሣጥኑ አስቀድሞ መገዛቱ ከፍተኛ ጥርጣሬ ፈጥሮባቸዋል።
በሕክምና ተቋማት የሞት ማረጋገጫ ወይም የቀብር ሰነድ አለመኖሩን ያረጋገጡት መርማሪዎች የባንክ እና የስልክ መረጃዎችን በመከታተል ግለሰቡ በሕይወት እንዳለ ደርሰውበታል።
ግለሰቡ በቁጥጥር ስር ውሎ የ አምስት ወር የእስራት ቅጣት እና የ 20,000 ዩዋን የገንዘብ መቀጫ ተጥሎበታል።
ወንጀለኛን በመሸሸግ እና እውነታውን በመደበቅ እናቱ እና አያቱም በህግ መጠየቅ ጀምረዋል ሲል የፃፈው ኦዲቲ ሴንትራል ነው።
ሔኖክ ወ/ገብርኤል
#Ethiopia #GetuTemesgen #GetuNews
#China #Drunk
#Odditycentral #Oddnews
Source: GetuTemesgen








No comments yet.