በ2018 በጀት ዓመት የሃይል ብክነትን ለመቀነስ 2.47 ሚሊዮን ቆጣሪዎችን መፈተሹን ያስታወቀው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ፤ ደንበኞች የቆጣሪ ንባባቸውን በራሳቸው ወደ ሲስተም የሚልኩበት የቴሌግራም መተግበሪያ በሙከራ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል ።
የአገልግሎቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው የ2018 በጀት ዓመት የእቅድ አፈፃፀም እና 2019 እቅድን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ ፤ በተደረገው የቆጣሪ ምርመራ 87 ሺህ 716 የተለያዩ ግኝቶች የተገኙ መሆኑን አንስተዋል ።
ይህም 1 ሺህ 493 ጊጋ ዋት በሰዓት የኢነርጂ ብክነት ወይም 2.89 ቢሊዮን ብር መሆኑን ገልፀዋል ። በተወሰደ የማስተካከያ እርምጃዎም 2.23 ቢሊዮን ብር ለተቋሙ ገቢ መሰብሰቡን አስረድተዋል ።
በተመሳሳይ የሀይል ስርቆት ፈፅመው የተገኙ 1 ሺህ 89 ግለሰቦችን በህግ ተጠያቂ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል ።
ተቋሙ በቴክኖሎጂ ዘርፍም 76 ሺህ 940 የደንበኞች ቅሬታዎች ተቀብሎ 71 ሺህ 676 ቅሬታዎችን በመፍታት 93.2 በመቶ አፈፃፀም እንዳስመዘገበ ጠቁመዋል ።
የደንበኞች ግንኙነት ማዕከሉን ወደ አዲስ ስርዓት በማሸጋገር በስልክ፣ በአጭር መልዕክት፣ በፌስቡክ፣ በዋትስአፕ እና በቴሌግራም አገልግሎት መስጠት መጀመሩንም ዋና ስራ አስፈፃሚው አስገንዝበዋል ።
በተጨማሪም ለቅድመ ክፍያና ድህረ ክፍያ ተጠቃሚዎች ኢ-ደረሰኝ ማግኘት የሚያስችል መተግበሪያ ስራ ላይ መዋሉን፣ የሃይል ስርቆትና የመሰረተ ልማት ጉዳት ሪፖርት ለማድረግ የ908 አጭር መልዕክት ስርዓት መጀመሩን ገልጿል ።
ከዚህ ባለፈም ደንበኞች የቆጣሪ ንባባቸውን በራሳቸው ወደ ሲስተም የሚልኩበት ኢኢዩ የቴሌግራም ቦት በሙከራ ላይ መሆኑን እንዲሁም የታቀዱና ያልታቀዱ የሃይል መቆራረጦችን የሚቆጣጠር ሲስተም ወደ ስራ መግባቱን አስታውቋል።
በስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ስራ 621 ጥቆማዎችና አቤቱታዎች መቀበሉን የገለጹት ዋና ስራ አስፈፃሚው ከእነዚህ 595 ላይ ምርመራ በማድረግ ምላሽ መሰጠቱን አንስተዋል ።
በምርመራው ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ 169 ሰራተኞች ውስጥ 166 ላይ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ፣ የደመወዝ ቅጣት፣ ከስራ ቦታ ማንሳትና ስንብትን ጨምሮ የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎች መወሰዳቸውንም አስረድተዋል ።
በመሰረተ ልማትና በንብረት ላይ የስርቆትና የውድመት ባደረሱ 124 ግለሰቦች ላይ ክስ ተመስርቶ እስከ 15 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ በፍርድ ቤት መወሰኑን አስታውቀዋል ።
#አሐዱ
Source: Yeneta Tube









No comments yet.