አገራት የሚፈርሱት በኢኮኖሚ

- Advertisement -
Sidebar AD

ሳይሆን በእምነት ማጣት ነው!

“መታመን ከመሥዋዕትነት ይበልጣል!” — ማርክ ካርኒ

እንደ መግቢያ

#Ethiopia | ይሄን መፅሐፍ ከሶስት ዓመት በፊት ገደማ አግኝቼ የተወሰነ ካነበብኩት በኋላ፣ በአንዱ ላይ ሌላውን እየደራረበ የሚቀጣጥለው የማያቋርጥ ሰበካና የጭብጦች መዓት አሰለቸኝ። ከሰላ ብዕረኛነት ወይ ከአሳማኝ ምሁራዊ ድርሰት ይልቅ፣ የካድሬ ዓይነት ወይ የቢሮክራት ዓይነት ዲስኩር መሠለኝ።

አላውቅም—ለምን እንደዚያ ሆኖ እንደታየኝ! በመሆኑም የሰውየውን እሴትን ያማከለ የመሪነት (Value-based Leadership) አስተሳሰብ፣ ጠንካራ የሞራል ሰብዕና፣ እንዲሁም የሰፋ ዕውቀቱንና ልምዱን አድንቄ መፅሐፉን አስቀመጥኩት። ባጭሩ፣ ማንበቡን ገታሁት።
ነገር ግን አሁን ድጋሚ አገኘሁት። መልሼ እያነበብኩት መደነቄ አልቀረም። የሚገርም ኤክስፐርት ነው! የተደነቀ የሃርቫርድና ኦክስፎርድ ዶክተር—ኢኮኖሚስት። በዓለማቀፍ ተቋማት ውስጥ ተረጋግቶ ማረጋጋትን በሚጠይቁ ትላልቅ ኃላፊነቶች ላይ ሠርቶ ብቃቱን ያስመሰከረ፣ ታምኖ የተከበረ ሰው ነው።

በማዕበል ውስጥ የቆመው መሪ

የ2008ቱ የምዕራቡ ዓለም የኢኮኖሚ ቀውስ ሲመጣ፣ የካናዳ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ሆኖ ካናዳን ከኢኮኖሚ መቅሰፍቱ በሽልም አወጣት። በ2018 ደግሞ የኮቪድ ምስቅልቅልና የብሬግዚት የኢኮኖሚ ገሞራ የእንግሊዝን ህልውና ሲያናውጠው፣ የባንክ ኦፍ ኢንግላንድ ገዢ ሆኖ በማዕበሉ ከመወሰድ አዳናቸው።

አሁን ደግሞ ከትራምፕ የሚመጣባቸው የኢኮኖሚ ነውጥና ተከታይ አደጋ ከፊታቸው ሲደቀን፣ ከእንግሊዝ አምጥተው የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር አደረጉት። በሚዋከብና በሚለዋወጥ ማዕበል ውስጥ ቀጥ አድርጎ፣ አረጋግቶ እየመራት ነው። እንዴ? እንዲህ ዓይነት ሰው ከየትኛው ፕላኔት ፈልገህ የምታገኘው ነው? ማርክ ካርኒ ነው ስሙ — ዶክተር ማርክ ካርኒ! ጉድ እኮ ነው።

አሁን ይሄን መፅሐፍ በሶስት ዓመት ውስጥ ለሶስተኛ ጊዜ አንስቼው እንዴት ልላቀቅ? ከኤአይ (AI) ቴክኖሎጂ እስከ ግዙፋን የንግድ ድርጅቶች፣ ከሰው ልጅ ስነልቦና እስከ ድኅረ-ዘመናዊ አስተሳሰቦች፣ ከተራቀቁ የሶሻል ሚዲያ አልጎሪዝሞች እስከ ክላሲካል ታሪክ፣ ኢኮኖሚክስ፣ ፖለቲካና ማህበራዊ ቲዎሪዎች — ሰውየው ሁሉንም ጠጥቶታል።

የቀደመውን መልክና ቁመናው፣ ንግግሩና ትህትናው ያማረውን መሪያቸውን ጀስቲን ትሩዶን ከዚህ የዚህችን ዓለም ፅድቅና ኩነኔ ምጥጥ አድርጎ ከበላ የዕውቀት ቀበኛ ሰው ጋር ስታነፃፅረው—አንድ ህፃን ልጅንና አንድ የታወቀ ፕሮፌሰርን ጎን ለጎን ቁጭ አድርገህ እንደማነፃፀር ያህል ሆኖ ይሰማሃል።

የውድቀትና የስኬት አከርካሪ — እምነት!

ያም ተባለ ይህ፣ ይሄ ደራሲ (እና ማዕበሉን ፀጥ የሚያደርገው ተዓምረኛ ሰው) ማርክ ካርኒ፣ በዚህ መፅሐፉ የሚዘረዝራቸውን የሕዝብና የመንግሥት አለመተማመን፣ የሀገር ውድመትና የኢኮኖሚ ክስረት ምክንያቶች ስታነብ ፈዝዘህ ትቀራለህ!

ምንጩ በትክክል ተፈላጊ በሆኑና በማያወላዱ እሴቶች ላይ ተመርኩዞ ሀገርን ለመምራት ያለመቻል — ባጭሩ የመሪነት ብቃት ማነስ — መሆኑን በምሁራዊ ኤክስፐርት ደረጃ የሚተነትንበት መንገድ በራሱ ለብቻው አንድ ትልቅ መፅሐፍ የሚወጣው ነው!

ለነገሩ ከካርኒ በፊትም ዴቪድ ጆንስተን የተባለው የቀድሞው የካናዳ ገቨርነር ጄነራል “Trust” በሚል መፅሐፉ ዘርዝሮ የፃፈው ነበረ። ግን ያ ይበልጥ ከግል ተሞክሮው ተነስቶ ለፖለቲካኞችና ለሀገር አስተዳዳሪዎች የሰጠው ምክር ነበር። “ትልቁ ነገር ዜጋችሁ እናንተን ያምናችኋል ወይ?” በማለት ነበር የሚያስረዳው። ዜጎች ባንተ ላይ ዕምነት ካጡ፣ በወስፌ ቅቤ ውጉልኝ ብትል እንኳ ይለግሙብሃል።

ማርክ ካርኒም ያንኑ ቁልፍ የአመራርነት አከርካሪ አጥንት ነው ደጋግሞ የሚያመላክተው። ግን በምሁራዊ በጥልቀት ነው፤ የተለያዩ ሞዴሎችን እያቀረበ፣ በሌሎች ተሞክሮ የሠራና የከሸፈን አካሄድ ከዓለም የቅርብና የሩቅ ታሪክ እያወጣ፣ ከራሱ ጥልቅ ልምድ ጋር አያይዞ ይተነትንልሃል። ፓ! ሲያስቀና! እኛ እንዲህ የሚገላግለን ሰው ከየት ይሆን አፈላልገን የምናገኘው?

Assaf Hailu


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: