#Fastmereja:-በኢትዮጵያ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነው ስትሪም አፍሪ የተሰኘ የላይቭ ስትሪሚንግ መተግበሪያ በይፋ መበለጸጉ በዛሬዉ እለት በተሰጠ መግለጫ ተገልጿል።
በዴላዌር ዩናይትድ ስቴትስ የተመዘገቡትና ዋና ሥራቸውን ከአዲስ አበባ የሚያካሂዱት ሁለቱ ተቋማት፣ የሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ባሉበት ሆነው የዓለም አቀፍ ገበያ ተደራሽነት እና ተቢውን የኢኮኖሚ ተፈጥሮ እንዲያገኙ ዓላማ አድርገው የተቋቋሙ መሆናቸዉ ተገልጿል።
በዚሁ መሠረት “ስትሪምአፍሪ” በስፖርት፣ በቱሪዝም፣ በትምህርት እና በኪነ-ጥበብ ዘርፍ የተሰማሩ የሀገርውስጥ ይዘት ፈጣሪዎችን፣ አርቲስቶችን እና አትሌቶችን ከዓለም ዙሪያ ካለው የዲያስፖራ ማህበረሰብ ጋር የሚያገናኝ ዘመናዊ የቀጥታ ስርጭት (Live Stream) መድረክ ነው።
በተለይም በቅርቡ በአደይ አበባ ስታዲየም የሚካሄደው የቦብ ማርሌይ ልጆች ኮንሰርት እና ድምፃዊ ቴዲ አፍሮ በጃማይካ የሚያቀርበው የሙዚቃ ኮንሰርት በዚሁ መተግበሪያ በቀጥታ ለዓለም አቀፍ ተመልካች እንደሚተላለፉ ተገልጿል።
በሌላ በኩል “ተስፋ ኤአይ” በሀገር ውስጥ የሚገነባውን የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ኢንጂነሪንግ ተሰጥኦ ለዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ለማቅረብ የተቋቋመ ሲሆን፤ የኤአይ አውቶሜሽን፣ ኤጀንቲክ መተግበሪያዎችን እና የርቀት የኢንጂነሪንግ ቡድኖችን ያቀርባል። ተቋሙ በተጨማሪም ዓለም አቀፍ ባለሙያዎችን ከሀገር ውስጥ ተሰጥኦዎች ጋር የሚያገናኝ የቀጥታ የትምህርት ቻናል በማንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝም ነዉ የተገለፀዉ።
የኩባንያዉ መስራች እና ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ናትናኤል ከበደ በሰጡት መግለጫ፤ “ነሐሴ 21 ቀን የሥራ ማስጀመሪያ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ይዘት ፈጣሪዎች እና ኢንጂነሮች ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ የሚደርሱበትን ክፍት መንገድ የምንፈጥርበት ታሪካዊ ቀን ነው” ብለዋል።
በመጪው ነሐሴ 21 በሚካሄደው የ«ሚክስ ማርሻል አርትስ» (MMA) ውድድር ወቅት በቀጥታ ስርጭት አገልግሎት መስጠት የሚጀምረው መተግበሪያ የቅድመ አባልነት ምዝገባ መጀመሩን አስታወቀ።
አገልግሎቱ በiOS፣ በAndroid እና በድረ-ገጽ (Web) ደረጃ የቀረበ ሲሆን፣ ይዘት ፈጣሪዎች ከወዲሁ ምዝገባ ማድረግ ይችላሉ ተብሏል።



Source: FastMereja









No comments yet.