የሱዳን ጦር አዛዥ ጄኔራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን፣ በሀገሪቱ የሚካሄደውን ጦርነት ተከትሎ ሁሉንም ወገኖች ያካተተ ብሔራዊ ምክክር ለማካሄድ ከፖለቲካ እና ከሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮችና ከተለያዩ ባለሙያዎች ጋር ይፋ ያልተደረገ ውይይት ማድረጋቸውን አልጀዚራ ዘግቧል።
በውይይቱ የተሳተፉ ወገኖች ለብሔራዊ ምክክር የሚያመች ሁኔታ ለመፍጠር በተወሰኑ ተግባራዊ እርምጃዎች መስማማታቸው ተገልጿል።
ከእነዚህም መካከል በፖለቲካ ተቃዋሚዎች ላይ የሚደረጉ የሚዲያ ዘመቻዎችን ማቆም እና በተቃዋሚ ፖለቲከኞች ላይ የተመሰረቱ የሞት ቅጣት ሊያስከትሉ የሚችሉ ክሶችን ማቋረጥ ይገኙበታል።
በተለይም በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ የሚመራው የሱዳን ፖለቲካ ጥምረት አባላትን ጨምሮ በበርካታ የፖለቲካ ተዋናዮች ላይ ክሶች መቅረባቸው ተጠቅሷል። ክሶቹም ከጦርነት ጋር በተያያዙ ወንጀሎች፣ ጦርነትን ማነሳሳት እና ሕገ መንግሥቱን ማፍረስ የሚሉ ክሶችን ያካትታሉ።
ለብሔራዊ ምክክር ከተለያዩ ወገኖች የተውጣጡ፣ በሰፊው ተቀባይነት ያላቸው ገለልተኛ ሰዎችን ያካተተ የዝግጅት ኮሚቴ እንዲቋቋም በውይይቱ ተስማምተዋል። ኮሚቴው የምክክሩን ተሳታፊዎች፣ አጀንዳ፣ ቦታና ጊዜ እንዲሁም የቀጠናውና ዓለም አቀፍ ታዛቢዎችን የመጋበዝ ሂደት እንደሚወስን ተገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም አል-ቡርሃን ከፖለቲካ ቡድኖች መሪዎች፣ ከባህላዊ መሪዎች፣ ከሃይማኖት መሪዎች፣ ከአካዳሚ ምሁራን ፣ ከተለያዩ ባለሙያዎች እና ከተቃውሞ ኮሚቴዎች ተወካዮች ጋር ስብሰባዎች ማድረጋቸው ተጠቁሟል። ዓላማውም ብሔራዊ መግባባትን ማጠናከርና ሁሉም የሚስማማበት ብሔራዊ ፕሮጀክት ላይ መድረስ መሆኑ ተገልጿል።
በሌላ በኩል፣ የተባበሩት መንግሥታት፣ የአፍሪካ ሕብረት፣ የአውሮፓ ሕብረት፣ ኢጋድ እና የአረብ ሊግን ያካተተው ቡድን በሱዳን የፖለቲካ ውይይት ለማስጀመር እየሰራ ቢሆንም፣ በፖለቲካ ቡድኖች መካከል ባሉ ልዩነቶች ምክንያት እስካሁን ተጨባጭ ስምምነት ማምጣት አልቻለም።
በተለይም በቅርቡ በአዲስ አበባ የተካሄደው ውይይት በሱዳን የፖለቲካ ቡድኖች መካከል ባለው አለመግባባት ምክንያት ውጤታማ ሳይሆን መቅረቱ ተዘግቧል።
የሱዳን ብሔራዊ ምክክርን ለማካሄድ ጥረት እየተደረገ ያለው የሱዳን ጦር እና ፈጣን ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች (RSF) የሚያደርጉት ጦርነት ሦስተኛ ዓመቱን በያዘበት ወቅት ሲሆን፣ የታቀደው ብሔራዊ ምክክር ጦርነቱን ለማስቆምና ወደ ፖለቲካዊ መፍትሔ ለመሸጋገር ዋነኛ የፖለቲካ መድረክ ይሆናል ወይስ አዲስ የፖለቲካ መካረር ይፈጥራል የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።
መረጃው የአልጀዚራ ነው።
Source: Yeneta Tube









No comments yet.