አጋዝእተ ዓለም ሥላሴ ከክፉ ነገር ሁሉ ይከልሉን፤ የልባችንን መልካም መሻትም ይሙሉልን

- Advertisement -
Sidebar AD

🙏

በኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 11፥1-9 እና በቅዱሳት አዋልድ መጻሕፍት ተጽፎ እንደምናገኘው ከጥፋት ውሃ በኋላ የኖኅ የትውልድ ነገዶች ከምሥራቅ ተነሥተው በሄዱ ጊዜ በሰናዖር ምድር አንድ ሜዳ አገኙ፤ በዚያም ተቀመጡ፤ ወልደው ተዋልደው ብዙዎች ሆኑ፡፡ በኋላም “ሳንሞት ስም ማስጠሪያ ግንብ እንገንባ” ብለው መከሩ፡፡ አለቃቸው ናምሩድም “ሞትን የሚያመጡብን ሥላሴ ናቸውና እነርሱን ወግተን ሞትን እናርቅ” አላቸው፡፡ ይህንም ለማድረግ ሰማይ ጠቀስ ግንብ ይገነቡ ጀመር፡፡ እግዚአብሔርም አለ “ኑ እንውረድ አንዱ አንዱን እንዳይሰማው በዚያ ቋንቋቸውን እንገለባብጠው”፡፡ ቅድስት ሥላሴ ምሕረታቸው የበዛ ቢሆንም በሕዝቡ ላይ ዲያብሎስ ስለሠለጠነባቸውና ለሌሎች ከሀድያን ትምህርት ይሆን ዘንድ ቋንቋቸውን ደበላለቁባቸው፡፡

እነርሱም የማይግባቡ፣ የማይደማመጡ፣ ሆነው ተበታትነዋል፡፡ ባለማስተዋል የሠሩትንም ሕንፃ ዓመጻ ነፋስ ጠራርጎ አጥፍቶታል፡፡ ያም ስፍራ ባቢሎን ተባለ። እነርሱንም በምድር ሁሉ ላይ በትኖአቸዋል። ይህን ያደረጉ ሥላሴ በመሆናቸው በዓሉ ጥር 7 ይከበራል፡፡ በዚህ የመጽሐፍ ክፍል ውስጥ “እግዚአብሔርም አለ” ብሎ አንድነቱን ከነገረን በኋላ “ኑ እንውረድ፤ አንዱ የአንዱን ነገር እንዳይሰማው ቋንቋቸውን በዚያ እንደባልቀው።” የሚል ከአንድ በላይ መሆንን የሚያመለክት ዓረፍተ ነገር ያስቀምጥልናል፡፡ ይህም በበርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የተገለጸ ሦስትነት እንደሆነ እንረዳለን፡፡ በዘፍ 1÷26 “እግዚአብሔርም አለ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር” የሚለው ቃል “እግዚአብሔርም አለ” ብሎ አንድነቱን “ሰውን በመልካችን እንፍጠር” ብሎ ልዩ ሦስትነትን ይገልጻል፡፡

ቅድስት ሥላሴ ተብለው በሴት አንቀጽ የሚጠሩት አጋእዝተ ዓለም ሥላሴ፣ በሴት መጠራታቸው የፍጹም ርህራሄያቸው፣ የቸርነታቸው ማሳያ ነው፡፡ አንድም ሦስትም ብላ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ታስተምረናለች፡፡ ይህ አንድነትና ሦስትነት እደምን ነው ቢሉ… በስልጣን፣ በአገዛዝ፣ በመለኮት፣ በሕልውና፣ በመፍጠር በመሳሰሉት አንድ ናቸው እንላለን፡፡ ልዩ ሦስትነታቸውም በስም “አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ” ብለን፣ በግብር “አብ ወላዲ ወይም አባት፣ ወልድ ተወላዲ ወይም ልጅ፣ መንፈስ ቅዱስ ሰራጺ፣ ከአብ የሰረጸ የወጣ” ማለት ነው፡፡ በአካል “ለአብ ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ ፍጹም መልክ አለው ነው፤ ለወልድም ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ ፍጹም መልክ አለው፤ ለመንፈስ ቅዱስም ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ ፍጹም መልክ አለው” ብለን እናምናለን፡፡

የሥላሴ ገጽ አካልና ፊት እንደ ሰው ነውን? የሚል ጥይቄ ቢነሣ መልሱ “አዎ፤ እንደ ሰው ነው” የሚል ነው፡፡ ነገር ግን የሰው ገጽ አካልና ፊት ውሱን፣ ጠባብ፣ ፈራሽና በስባሽ ነው፤ የሥላሴ ግን እንዲህ አይደለም፤ በሰማይና በምድር፣ በአየርና በእመቅ የመላ ረቂቅ ሕያው ባሕርይ ነው፡፡ ታላቁ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ኢሳይያስ በምዕራፍ 86÷1-2 እንደጻፈው “ሰማይ ዙፋኔ ነው፤ ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ የምትሠሩልኝ ቤት ምን ዓይነት ነው? የማርፍበትስ ስፍራ ምንድን ነው? ይህ ሁሉ የእጄ ሥራ ነው፤ ይህም ሁሉ የእኔ ነው” ይለናል በአንድነት በሦስትነት የሚመሰገን የሚመሰጠር ቅዱስ እግዚአብሔር፡፡

በዚህ ልዩ ሦስትነት አምነን የተጠመቅንና እኛ ክርስቲያኖች የሥላሴን በረከት ለመቋደስ በበረከት ስራ እንሳተፍ፡፡ የትምህርቱ ምንጭ የሆኑትን ገዳማት እንርዳ፣ የገዳማውያኑን በዓት እናጽና፡፡

ድጋፍ ለማድረግ:- ሙትአንሳ ማር ቅዱሰ ሚካኤል አንድነት ገዳም

ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ
1000442598391

ወይም

አቢሲኒያ ባንክ
141029444

ለበለጠ መረጃ:- 09 38 64 44 44/0918077957


Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1