#Ethiopia | በኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን አዘጋጅነት የዓለም አቀፍ የባህል ስፖርቶች እና ጨዋታዎች ቀን ዛሬ ነሐሴ 08 ቀን 2018 ዓ.ም በሀገራችን በታላቅ ስነ-ስርዓት ተከብሯል።
በጊዮን ሆቴል በተካሄደው በዚህ መርሃ-ግብር ላይ የአፍሪካ ባህል ስፖርቶች እና ጨዋታዎች ኮንፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ህይወት መሀመድ፣ የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ አባል እና የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ይልማ መንግስቱ፣ የስፖይን ኮንሶልታንሲ ባለቤት አቶ ዮናስ እንዲሁም የብዙኃን መገናኛ ተወካዮች ተገኝተዋል።
በስነ-ስርዓቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ወ/ሮ ህይወት መሀመድ፣ የባህል ስፖርቶቻችን የስፖርት እና የመዝናኛ መድረክ ከመሆናቸው በላይ የኢትዮጵያውያን የማንነት፣ የሕያው ታሪክ፣ የኪነ-ጥበብ እና የህብረ-ብሔራዊ አንድነት መግለጫዎች መሆናቸውን አብራርተዋል።
ፕሬዝዳንቷ አክለውም፣ ኢትዮጵያ የብዙ ብሔሮች እና ብሔረሰቦች መኖሪያ እንደመሆኗ መጠን እነዚህ ውድ ባህላዊ ስፖርቶች በትውልዶች መካከል ድልድይ በመሆን ማህበራዊ እሴቶችን እና ትስስርን ሲያጠናክሩ መኖራቸውን በመግለጽ ስፖርቶቹ ከሰዎች ዕለታዊ ሕይወት እና ማህበራዊ እድገት ጋር ያላቸውን ጥልቅ ቁርኝት አመልክተዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረው ይህ ዕለት ባህላዊ ስፖርቶች በዓለም ህዝቦች መካከል ለሚፈጠር መቀራረብ፣ መስተጋብር እና የሰላም እሴቶች ግንባታ ያላቸውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለማሳወቅ የተሰየመ መሆኑ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን እነዚህን ሀገር በቀል እሴቶች የማጥናት፣ የመጠበቅ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የማስተዋወቅ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።
በዓሉ ሲከበርም እነዚህ ስፖርቶች በየአካባቢው ብቻ ተወሰነው እንዳይቀሩ ዘመናዊ አሰራርን ከተላበሱ ስፖርቶች ጋር ጎን ለጎን በማሰለፍ ለስፖርታዊ ውድድር እና ለባህል ቱሪዝም እንዲያውሉ ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት በማረጋገጥ ነው።
ስለሆነም የሀገርን መልካም ገጽታ ለመገንባት፣ ባህላዊ ቱሪዝምን ለማሳደግ እና ለወጣቶች ሁለንተናዊ እድገት አስተዋጽኦ ያላቸውን እነዚህን የባህል ስፖርቶች እንክብካቤ በማድረግ ለተተኪው ትውልድ ማስተላለፍ የሁሉም አካላት የጋራ ኃላፊነት እንደሆነ መልዕክት ተላላፏል።
የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ አባል እና የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ይልማ መንግስቱ በበኩላቸው፣ የዚህ ቀን መከበር ለሀገራችን ባህላዊ ስፖርቶች እድገት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
የስፖይን ኮንሶልታንሲ ባለቤት አቶ ዮናስም ተቋማቸው የዚህ ታሪካዊ መርሃ-ግብር አካል በመሆኑ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው የፌዴሬሽኑን ጥረት አደንቀዋል።
በመጨረሻም ፌዴሬሽኑ የባህል ስፖርቶችን በዓለም አቀፍ መድረክ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጽ መርሃ-ግብሩ በደማቅ ሁኔታ ተጠናቋል።
#traditionalsports #ethiopiansports #culture #tourism #ethiopia #getutemesgen #getu #ጌጡ #ጌጡተመስገን #addisababa



Source: GetuTemesgen









No comments yet.