በህክምና ምርምር ተነስቶ የሒሳብ ታሪክ የሰራው ቻይናዊ ዶክተር እና የቻት ጂፒቲው ተዓምርቤጂንግ ውስጥ የሚኖረው የአዕምሮ እና …

- Advertisement -
Sidebar AD
በህክምና ምርምር ተነስቶ የሒሳብ ታሪክ የሰራው ቻይናዊ ዶክተር እና የቻት ጂፒቲው ተዓምር
ቤጂንግ ውስጥ የሚኖረው የአዕምሮ እና ነርቭ ቀዶ ህክምና ሃኪም ጂን ሻንሙ የኮምፒውተሩን ስክሪን ሲከፍት የሒሳብ ታሪክ ለመስራት አስቦ አልነበረም። የሱ ዋነኛ ፍላጎት ከአዕምሮ አልትራሳውንድ (brain ultrasounds) ጋር የተያያዘ አንድ የህክምና ችግርን መፍታት ብቻ ነበር።
ነገር ግን ይህ በራሱ ጥረት ሒሳብን ያጠናው ሃኪም፣ የኦፕን ኤአይ የቅርብ ጊዜ ቴክኖሎጂ በሆነው አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) በመታገዝ፣ በመላው ዓለም ያሉ ባለሙያዎችን ለሁለት አስርት ዓመታት ሲፈትን የነበረውን አበይት የሒሳብ እንቆቅልሽ ባልታሰበ ሁኔታ መፍታት ችሏል።
ጂን ይህንን ከ2004 ጀምሮ ያልተፈታውን እና በዘርፉ ባለሙያዎች ዘንድ ‘ክሩዜክስ ኮንጀክቸር’ (Crouzeix’s conjecture) በመባል የሚታወቀውን ውስብስብ የሒሳብ ቀመር የፈታው፣ በቻት ጂፒቲ መድረክ ላይ የሚሰራውን “ጂፒቲ-5.6-ሶል” የተሰኘውን አዲስ የኤአይ ሞዴል ለ16 ሰዓታት ያህል ራሱን ችሎ እንዲሰራ በማድረግ ነው።
ፈረንሳዊው የሒሳብ ሊቅ ሚሼል ክሩዜክስ ያቀረበው ይህ ፅንሰ ሃሳብ እጅግ ረቂቅ ቢሆንም፣ ዶክተሩ በምርምሩ ላይ ባጋጠመው አጋጣሚ ተጠቅሞ ዓለምን ወዳስደመመ ታላቅ ግኝት ላይ ደርሷል።
ይህ አስገራሚ ግኝት ይፋ የሆነው፣ የኮርኔል ዩኒቨርሲቲው የሒሳብ ሊቅ አሌክስ ታውንሴንድ እና የዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲዋ ፕሮፌሰር አን ግሪንባም ከቻይናዊው ዶክተር ጋር ያደረጉትን የኢሜይል ልውውጥ ይፋ ባደረጉበት ወቅት ነው።
ታውንሴንድ ይህንን የሒሳብ እንቆቅልሽ ለመፍታት ለአንድ ዓመት ሙሉ የጂፒቲ ሞዴሎችን ሲጠቀም የቆየ ቢሆንም፣ ባሳለፍነው ሀምሌ ወር መጨረሻ አካባቢ አርቲፊሻል ኢንተለጀንሱ ያልተጠበቀ ምላሽ ሰጠው።
ይኸውም ጂን የተባለው ሃኪም ችግሩን እንደፈታው የሚያሳይና ከሶስት ቀናት በፊት በበይነመረብ ላይ የተጫነን ጥናታዊ ፅሁፍ ጠቆመው።
እነዚህ ታዋቂ የሒሳብ ሊቃውንት እና ራሱ ፅንሰ ሃሳቡን ያመነጨው ክሩዜክስ የዶክተሩን ፅሁፍ ገምግመው የስሌቱ ሂደት ሙሉ በሙሉ ትክክለኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ጂን በመጀመሪያ ዲግሪው የጂኦሎጂ ተማሪ የነበረና በኋላ ወደ ህክምና የገባ ሲሆን፣ መሠረታዊ ከሚባለው የሳይንስ ትምህርት ውጪ የሒሳብ ትምህርትን በራሱ ጥረት ብቻ ያዳበረ ሰው መሆኑ የኤአይ (AI) ቴክኖሎጂን አስደናቂ አቅም በጉልህ አሳይቷል።
ይህ ክስተት ዘመናዊው አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በዓለማችን ለረጅም ጊዜ ያልተፈቱ እንደ 1946ቱ የሃንጋሪያዊው ፖል ኤርዶስ ቀመር እና እንደ ሪማን ሃይፖቴሲስ የመሳሰሉ ጥልቅ የሒሳብ ስሌቶችን ለመፍታት እያበረከተ ያለውን ጉልህ አስተዋፅኦ በተግባር ያረጋገጠ አስደናቂ የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ ተመዝግቧል።
@Seledadotio
@Seledadotio

Source: SeledaPost

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1