#Ethiopia | አቴንስ (ነሐሴ 9)፦ በግሪክ ቲኖስ ደሴት በሚገኘው ታዋቂው የፓናጊያ ኢቫንጀሊስትሪያ (Panagia Evangelistria) ቤተ ክርስቲያን የቅድስት ድንግል ማርያም የዕረፍትና የእርገት በዓል (Dormition of the Mother of God) የሁለት ሱባኤ የጾመ ፍልሰታ ማጠቃለያን አስመልካች በታላቅ ሃይማኖታዊና ብሔራዊ ሥነ-ሥርዓት እየተከበረ ይገኛል።
እ.ኤ.አ የነሐሴ 15 qN 2026 በዓል በግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ «የበጋው ፋሲካ» በመባል የሚታወቅና እመቤታችን ከምትዘከርባቸው ዋና ዋና በዓላት አንዱ ሲሆን፣ በቲኖስ ደሴት በተለይ ታላቅ የጸሎትና የቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ይካሄድበታል።
ቲኖስ በግሪክ ኦርቶዶክሳውያን ዘንድ ከፍተኛ የምዕመናን መዳረሻና የመንፈሳዊ በረከት ስፍራ በመሆኑ፣ በዓሉ ላይ ከመላዋ ግሪክና ከዓለም አቀፍ ኦርቶዶክሳውያን ሀገራት የተሰበሰቡ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ምዕመናን ታድመዋል። ቀኑ በሀገሪቱ ብሔራዊ የዕረፍት ቀን በመሆኑ የግል ሱቆችን ጨምሮ ተቋማት ተዘግተው ሕዝቡ ወደ ቤተ ክርስቲያን ያመራል።
የቲኖስ ተአምረኛዋ ሥዕለ አድኖ የበዓሉ ሃይማኖታዊ ማዕከል የሆነችው የፓናጊያ ኢቫንጀሊስትሪያ ቤተ ክርስቲያን በስፋት የምትታወቀው በውስጧ በሚገኘው ተአምረኛው የእመቤታችን ይቅድስት ማርያም ቅዱስ ሥዕል አድኖ ነው።
በአካባቢው የቤተ ክርስቲያን ታሪክና ትውፊት መሠረት እህት ፔላጊያ የተባሉ ግሪካዊት ኦርቶዶክሳዊት መነኩሲት እ.ኤ.አ. በ1822 በተደጋጋሚ እመቤታችን በራዕይ ከተገለጠችላቸው በኋላ ሥዕሉ በመሬት ውስጥ እንደተቀበረ በመግለጽ ፍለጋው እንዲጀመር የመንፈሳዊ መሪነት ሚናውን ተወጥተዋል።
በዚህም መሠረት እ.ኤ.አ. በጥር 30 ቀን 1823 ዓ.ም. በተደረገው ቁፋሮ ድንቅ ተአምር ያለው የእመቤታችን ቅዱስ ሥዕል ሊገኝ ችሏል።
ይህ ሥዕል መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የብስራት ቃል የሚያበስርበትን ምስል (Annunciation) የሚያሳይ ሲሆን፣ ሥዕለ አድኖው በተገኘበት በዚህ ቅዱስ ስፍራ ላይም የአሁኑ ቤተ ክርስቲያን ሊገነባ ችሏል።
በዚህ መንፈሳዊ ታሪክ ምክንያት ቲኖስ ለመላው ግሪክ ኦርቶዶክስ ምዕመናን ከፍተኛ የጸሎትና የምስጋና ማቅረቢያ ስፍራ ሆኗል። በተለይም በየዓመቱ በነሐሴ 15 በዓል ላይ ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ ምዕመናን ለጸሎት፣ ለበረከትና በየአመቱ የሚሳሉትን ስእለት ለማስገባት ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ይተማሉ።
የበዓሉ ዋና ሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓት በበዓሉ ዋዜማ በቤተ ክርስቲያኑ በፓትርያርኩና በኤጲስ ቆጶሳት የሚመራ ታላቅ የቅዳሴና የጸሎተ ኪዳን ሥነ-ሥርዓት የሚካሄድ ሲሆን፣ በዕለቱም በሊቃነ ጳጳሳትና ካህናት ታጅቦ ሁሉም ምእመናን በተገኙበት ቅዳሴ ይቀደሳል።
ከቅዳሴው በኋላ ተአምረኛውን ቅዱስ ሥዕል የማንቀሳቀስና የማጠንም ታላቅ የቡራኬ ሰልፍ ይካሄዳል። ሥዕሉን በልዩ ክብር በመሸከም ከቤተ ክርስቲያኑ ወጥቶ በምዕመናን መካከል ሲዞር የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የመንግሥት አባላትና የግሪክ የባሕር ኃይል አባላት በክብር ዘብነት መሳተፋቸው የበዓሉ ልዩ ገጽታ ነው።
በተጨማሪም ብዙ ምዕመናን የተቀበሉትን ጸጋና የተደረገላቸውን ተአምር በማሰብ ስእለታቸውን ለመፈጸም ከደሴቷ ወደብ አንስቶ እስከ ቤተ ክርስቲያኑ በር ድረስ ያለውን ረጅም ኮረብታማ መንገድ በእግራቸው፣ አንዳንዶቹም በታላቅ ትህትና በጉልበታቸውና በእንብርክካቸው እየሄዱ ይደርሳሉ። ይህ ተግባር በቲኖስ ደሴት ከሚታወቁት ታላላቅ የሃይማኖትና የስእለት ልማዶች አንዱ ነው።
ከሃይማኖታዊ ትርጉም ባሻገር
የቲኖስ ነሐሴ 15 በዓል ጥልቅ ሃይማኖታዊ ገጽታ ያለው ከመሆኑ ባሻገር፣ ከዘመናዊቷ የግሪክ ታሪክና ከብሔራዊ መታሰቢያዎች ጋርም የተያያዘ ነው።
እ.ኤ.አ. በ1940 ነሐሴ 15 ቀን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በቲኖስ ወደብ የቆመችው የግሪክ የጦር መርከብ “ኤሊ” (Elli) በቶርፔዶ መመታቷ በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ ከሚታወቁ አሳዛኝ ክስተቶች አንዱ ነው። በመርከቡ ላይ የነበሩ የሠራዊት አባላት ሕይወታቸውን ማጣታቸውም በየዓመቱ በቲኖስ በዓል ዕለት የሚዘከር ታሪካዊና ብሔራዊ ክስተት ሆኗል።
በዚህም ምክንያት ነሐሴ 15 በቲኖስ የሚከበረው በዓል መንፈሳዊ ሃይማኖትን፣ የታሪክ ሁነቶችንና የብሔራዊ ትውስታ አካላትን አስተሳስሮ የያዘ ታላቅ በዓል ለመሆን በቅቷል።
ቲኖስ—የምዕመናን መንፈሳዊ መዳረሻ
ዛሬም የፓናጊያ ኢቫንጀሊስትሪያ ቤተ ክርስቲያን በግሪክ ኦርቶዶክስ ዘንድ ከፍተኛ የጸሎትና የመንፈሳዊ በረከቶች መዳረሻ ሆና ትገኛለች። ቤተ ክርስቲያኑ በቅዱስ ሥዕሉ መገኘት ዙሪያ ከተፈጸሙ ተአምራት፣ ከምዕመናን ጥልቅ ስእለትና ከረዥም ዘመን የቆየ ሃይማኖታዊ ባህል ጋር ተያይዞ የመላው ግሪክ ኦርቶዶክስ ሕዝብ በታላቅ አክብሮት ከሚያያቸው ቅዱሳን ስፍራዎች አንዷ ናት።


Source: GetuTemesgen









No comments yet.