የቦሌ ልጅ ነኝ!

- Advertisement -
Sidebar AD

ሳ’ምባዲ ሴይ “ቦሌ ቦሌ” አለ ሮፍናን ?
በመላኩ ብርሃኑ ተጻፈ
*****

ባይ ዝዋይ … የቦሌ ልጅ ነኝ። ( ማለቴ እኔ የተወለድኩበት ሰፈር ድሮ ቦሌ ነበር የሚባለው) ።አሁን ደምበል ምናምን እያላችሁ ባልዋለበት እያዋላችሁት እንጂ ሰፈሬ ቦሌ ነበር። …. መድሃኔአለም ቤተክርስቲያን አካባቢ የሚገኘው ሰፈር “ቦሌ” የሚለውን መጠሪያ ነጥቆ ሲወስድብን ሰፈሬ ሚናዋን ለይታ “ኦሎምፒያ” የሚለውን የቀድሞ መጠሪያዋን የሙጥኝ አለች …

I Love it! ይስማማኛል…

የምር ግን …ድሮ እኮ ከፍላሚንጎ በታች፣ ከቦሌ ሚኒ በላይ ያለው ሰፈር ሁሉ ‘ቦሌ’ ይባል ነበር። መንገዱም “ቦሌ መንገድ” ነበር የሚባለው። እናቶቻችን ሲመርቁም ሲራገሙም “የቦሌ አድባር ትቅናህ…የቦሌ አድባር ድፍት ታድርግህ” እያሉ ነበር። በቦሌ አስፖልት ወክ እያደረጉ የቦሌን አየር ለመተንፈስ ስንትና ስንቱ ከየትና የት ሰፈር በባስ እየተሳፈረ ነበር እኛ ሰፈር ድረስ የሚመጣው።የዛሬን አያድርገውና።

እናም …”የቦሌ ልጅ በመሆኔ ብቻ በፊትበር ልጆች የተደበደብኩ ሰው ነኝ” ልላችሁ ነው።

ያኔ ፊትበር (አሁን ሸራተን አዲስ የተገነባበት ቦታ) “ሞጋ” ብለን የምንጠራውን የጎማ ጫማ የሚሰሩ ሰዎች ነበሩ። ሞጋ በሌላ ሰፈር ልጆች ዘንድ “በረባሶ” በሚል ስም ይታወቃል። አመጣጡን ሳጠና አቶ ሞጋ የሚባሉ አንድ የፊትበር ኗሪ የሆኑ የደቡብ ሰው በዚህ ጫማ ስራ እውቅ በመሆናቸው የጫማው ብራንድ በሳቸው ስም እንደተሰየመ ደርሼበታለሁ።

እና አንድ ቀን ክረምት ላይ ኳስ ለመራገጫ የሚሆን ሞጋ ለማሰራት ከሰፈር ልጆች ጋር ተሰብስበን ፊትበር ሄድን። የፊትበር ‘ዱርዬዎች’ አገኙንና አስቆሙን። ያኔ’ኮ የአዲስ አበባ ሰፈሮች የየራሳቸው ‘ድንበር ጠባቂ’ ብርጌድ ጦሮች ነበሯቸው። የፊትበር ልጆችም ታዋቂ ጸበኞች ነበሩ በጊዜው።ጩቤ ይዘናል ለማለት እጃቸውን ወገባቸው ውስጥ ሻጥ ሻጥ እያደረጉ አስፈራሩንና አስቆሙን።

“እያንዳንድሽ የያዝሽውን ፍራንክ ከች አድርጊ” ተባልን።

ብዙዎቻችን ለሞጋው ማሰሪያ ቡሄ ጨፍረን የሸቀልናትን ከርክ እና ቼላ ብቻ ነበር በኪሳችን የያዝነው።ከርክ ከቼላ። 75 ሳንቲም ማለት ነው።

አጅበውን ከሄዱት ደግሞ ዲናሬም ሲታም ዱዲም የያዙ የሰፈር ልጆች ነበሩ። ቀዳዳ ኪሶችም ብዙ ነበሩ።

( አራድኛ ነቄ ያለ ሰው ይተርጉምላችሁ😜🤪)

ኪሳችንን ካራገፉ በኋላ “ሰፈራችሁ የት ነው ?!” ብለው ጠየቁን። ያኔ ዑራኤል፣ ቄራ ምናምን ሰፈሮች የጸበኛ ሰፈሮች ነበሩና ከነዚህ ሰፈር የመጣውን ሰው ስጋውን ቀርቶ ነፍሱን አይተዉለትም ። የኛ ሰፈር ግን ሰላማዊ ሰፈር ነው። በጸብ የሚያውቀው ማንም የለም። እኔን የመሳሰሉ ለሃገርና ለዓለም የተረፉ ጨዋዎች የወጡበት ሰፈር ነው (ቂቂቂቂቂ ….ዋሸሁ እንዴ?)

ስለዚህ ብዙም አልደነገጥንም። “ከቦሌ” አልን። “ጥፉ ከዚህ” ብለው እንደሚለቁን እርግጠኞች ነበርን።ያሰብነው ግን አልሆነም። መሪያቸው ከላይ እስከታች አይቶን ጭራሽ ተናደደ።

” እናታችሁን ‘እንትን ልበልላችሁ’። ማናባታችሁን ልትሸውዱ ነው…የታል ስኒከር ያደረጋችሁት ?… ሌዘር ምናምኑ የታል…

በንዴት ሱሪያችንን አስወልቆ ቡታንታችንን ጭምር ፈተሸን። (በርግጥ ብዙዎቻችን ፓንት የለንም 😂)

ምንም ሲያጣ የበለጠ ተናደደ። “እናታችሁን! የቦሌ ልጅ ደሞ ሞጋ ያደርጋል? … ደሃ ሁሉ ” አለና በያዘው የሰንሰል ልምጭ እየለጠለጠ ሁለተኛ ፊትበር ሰፈር እንዳንደርስ ሲያስጠነቅቀን በቀላሉ ስለተወን ደስ ብሎን ከልምጩ ለመሸሽ መሮጥ ጀመርን። ሁሉም ተከተሉን።

ከዚያ የሮጥን በቤተመንግስት ቁልቁል አድርገን ፍላሚንጎ ስንደርስ ነው ልባችንን ደግፈን ቁጭ ቁጭ ያልነው።

(የፊት በር ልጆች…ዛሬ ጸሃዩ መንግስታችን ከስራችሁ ንቅል አድርጎ የበታተናችሁ ወላጆቻችን ገንዘብ እንደቀማችሁን ስንነግራቸው “የቦሌ አድባር ትንቀላቸው!!” ብለው ረግመዋችሁ መሆኑን ስነግራችሁ በታላቅ ትህትና ነው 😆😆)

ያኔ እንግዲህ የቦሌ ልጅ ማለት የሃብታም ልጅ እንደማለት ነው። ቦሌ ደግሞ በአፍሪካ ጎዳና የተዘረጉትን ከኦሎምፒያ ጀምሮ … ቦሌ ማተሚያ ቤትን ይዞ ..ግን ደግሞ ወሎ ሰፈርን ዘልሎ (ቂቂቂቂ) … እስከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ድረስ ያሉትን…በተለይ ደግሞ አሁን ሩዋንዳ ከሚባለው አካባቢ ጀምሮ የተሰሩትን ….አንድ አንድ ሺህ ካሬ ምናምን የሞጃ ግቢ የበዛባቸው ሰፈሮችን ያጠቃልላል። ስኒከር ጫማ፣ ማይክል ጂንስ ሱሪ…ነጫጭ ቲሸርት… ሌዘር ጃኬት ምናምን የዚያ ሰፈር ልጆች ልብስ ነበር። የሞጃ ልጆች መለያ ።ከአሜሪካ ይመጣላቸዋላ!

እኛ ለራሳችን ሙልጭ ያልን የደሃ ልጆች …በሸርተቴ ጨዋታ “የሱሪያችን ቂጥ” መነጽር የሰራብን..በመነጽሩ ስር ቀይ፣ ጠይም፣ ጥቁር ቂ*ችን አቧራ ቅሞ የሚታይብን ….ቂቂቂቂ… ግን ደግሞ የቦሌ ልጆች ነን የምንል ነበርን ።

ቦሌ ማለት እንግዲህ በስሟ የተገረፍንላት፣ ከነጨርቆስና ፊት በር አይነት ሰፈሮች ‘በኮምፕሌክስ’ ምክንያት መግቢያ ቪዛ የተከለከልንባት፣ ከግሩፕ ጸብ ለማምለጥ ማራቶን የሮጥንባትን ሰፈራችን ናት ።

እና ምን ለማለት ነገር ኖ?

ሮፍናን …ሳ’ምባዲ ሴ’ይ… ሲል የዚህም የዚያም ሰፈር ልጆች ተሽቀዳድማችሁ “ቦሌ ቦሌ” አትበሉ።

Bole isn’t your ሰፈር at all… It’s me who belongs to ቦሌ!

ኪሏችሁን” እንደፈለጋችሁ ጥሯት..ኣ?!

በነገራችን ላይ በኦሮምኛ “ቦሌ” ማለት ሜዳ ማለት ነው አሉ። የከብቶች ግጦሽ ሜዳ። ቂቂቂ

ዘሩ ሲዘረዘር .. ቦሌ ቡልቡላ ፣ ቦሌ አራብሳ፣ ቦሌ ወረገኑ፣ ቦሌ ኮተቤ፣ ይልና በመጨረሻም ቦሌ ብቻውን …የኛ ሰፈር ይሆናል ።

ይመቻችሁ የቦሌ ልጆች!!


Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2