#Ethiopia | በኢትዮጵያ በሴቶች እና በህፃናት ላይ የሚፈጸመውን ፆታዊ ጥቃት፣ ግድያ እና እንግልት በመቃወም “#ትሰማ” (#Tisema) በሚል ሃሽታግ የተቀናጀ የዲጂታል ዘመቻ ተጀምሯል።
በርካታ ማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ይፋዊ የማህበራዊ ድረ-ገጾች በመልዕክት እያጠለቀለቁ የሚገኙ ሲሆን መንግስት በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን እና ግድያዎችን እንደ “አገር አቀፍ ቀውስ” አውጆ አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጥ እየጠየቁ ነው።
ይህ ንቅናቄ የፌደራል በጀት የተመደበለት ሀገራዊ አስተባባሪ መስሪያ ቤት እንዲቋቋም እና ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥ አሰራር በጊዜ ገደብ እንዲዘረጋ ጥሪ ያቀርባል።
ይህ አገር አቀፍ ቁጣ እንዲቀሰቀስ ምክንያት ከሆኑት አሳዛኝ ድርጊቶች መካከል በባህር ዳር ከተማ አስገድዶ የተደፈረችውና የተገደለችው የሰባት ዓመቷ ህፃን ሄቨን አወቀ ጉዳይ አንዱ ሲሆን፣ ፍትህ ለማግኘት ከሶስት ዓመታት በላይ የፈጀው የፍርድ ቤት ሂደት ህዝባዊ ቅሬታን ፈጥሯል።
ከዚህ በተጨማሪም እንደ ዘውዱ ሃፍቱ፣ ቀነኒ እና ሊዛ ያሉ በርካታ ሴቶች የደረሰባቸው አሰቃቂ ጥቃት እና ህጋዊ ፍትህ መዘገየት የፍትህ ስርዓቱ ጥቃቶችን ለመግታትና ተበዳዮችን ለመጠበቅ ያለበትን ክፍተት ያሳየ ነው ብለዋል።
በግጭቶች ምክንያት ጥቃት የደረሰባቸው ከ300 ሺህ በላይ ሴቶች፣ ያለዕድሜ ጋብቻ እና እገታዎች በየጊዜው የሚሰሙ አሳዛኝ ክስተቶች መሆናቸው ተገልጿል።
የዘመቻው አስተባባሪዎች እንደሚገልጹት ፆታዊ ጥቃት ከግድያ በፊት ከሚጀመሩ ትንኮሳዎች እና የቤት ውስጥ ጥቃቶች የሚመነጭ በመሆኑ አጠቃላይ መፍትሄ ያስፈልገዋል።
ተመሳሳይ ህዝባዊ ንቅናቄ በደቡብ አፍሪካ ተካሂዶ ከ1 ሚሊዮን በላይ ፊርማ ከተሰበሰበ በኋላ ያለፈው ዓመት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጉዳዩን የብሔራዊ አደጋ አድርገው ማወጃቸው ይታወሳል።
በአሁኑ ወቅት በአዲስ ፓወርሃውስ በኩል የኦንላይን አቤቱታ ፊርማ ማሰባሰብ የተጀመረ ሲሆን ህብረተሰቡ ፊርማውን በመፈረም እና መልእክቱን በማጋራት የሴቶችን ድምፅ እንዲያሰማ ጥሪ ቀርቧል።
በያፌት ገ/ህይወት
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu
Source: GetuTemesgen






No comments yet.