“ትምህርት ገንዘብ ዝም ብሎ የሚሰበሰብበት ተራ ንግድ አይደለም!” አሉ ዶ/ር ነገሬ ሌንጮ

- Advertisement -
Sidebar AD

በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ላይ የተጋረጠው የጥራት ቀውስ እና በመንግሥት ቁጥጥርና በግል ተቋማት ነጻነት መካከል ያለው ፍጥጫ አደባባይ ወጥቷል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዳራሽ ነሐሴ 08 /2018 ዓ.ም የተካሄደው የቋሚ ኮሚቴ ውይይት፣ በዘርፉ ላይ ለዓመታት ታፍነው የቆዩ ቅሬታዎችና የፖሊሲ መገፋፋቶች የፈነዱበት መድረክ ነበር።

ውይይቱን በንግግር የከፈቱት ዶ/ር ነገሬ ሌንጮ፣ ወደ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች ጣታቸውን በመቀሰር መረር ያለ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

“ትምህርት ገንዘብ ዝም ብሎ የሚሰበሰብበት ተራ ንግድ አይደለም!” ያሉት ሰብሳቢው፣ ዘርፉ ከፍተኛ ኃላፊነትና ተጠያቂነት የሚጠይቅ ስልታዊ ኢንቨስትመንት መሆኑን አስምረውበታል።

እንደ እሳቸው አገላለጽ፣ መንግሥት የሚፈልገው ተቋማት ተዘግተው ሥራ አጥነት እንዲነግስ ሳይሆን፣ “ሰርተፊኬት ብቻ ተሸክሞ የሚዞርና ለሀገር ሸክም የሚሆን ዜጋ” የማፍራቱ ሂደት እንዲቆም ነው። ይህ ንግግር በትርፍ ላይ ብቻ ለሚያተኩሩ ባለሀብቶች የተላከ ግልጽና መራራ መልእክት ይመስላል።

በሌላ በኩል፣ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማህበር ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሞላ ፀጋዬ፣ በመንግሥት በኩል የሚወጡ መመሪያዎች “አሰራሪ ሳይሆኑ አሳሪ” መሆናቸውን በምሬት ገልጸዋል።

ተቋማቱ በዳግም ምዝገባ ወቅት የሚገጥማቸው ፍትሐዊ ያልሆነ መመዘኛ፣ ለመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች የፒ.ኤች.ዲ (PhD) መምህራንን ቅጠሩ የሚለው አስገዳጅ ሕግ፣ እና ስለ ግቢ ስፋትና በግቢ ውስጥ ስለሚኖሩ አገልግሎቶች የተቀመጡት “ጠባብ” መመሪያዎች ዘርፉን አጣብቂኝ ውስጥ ከትተውታል ብለዋል።

“ባንክ በሌለበት ዩኒቨርሲቲው አይታደስም” የሚሉ አይነት ጥብቅ መመሪያዎች ተቋማቱን ለኪሳራና ለሥራ ማቆም እየዳረጓቸው መሆኑን በዝርዝር አቅርበዋል።

የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አህመድ አብተው ግን ለቅሬታዎቹ እጅ አልሰጡም።
መመሪያዎቹ የወጡት ለተቋማቱ ማነቆ ለመሆን ሳይሆን የኢትዮጵያን ተማሪዎች መብት ለማስከበር መሆኑን በጽኑ ተከራክረዋል።

“ተማሪው ጥራት ያለው ትምህርት፣ ቤተ-ሙከራና ቤተ-መጽሐፍት በአቅራቢያው የማግኘት መብት አለው” ያሉት ዳይሬክተሩ፣ የትምህርት ጥራት ላይ ምንም አይነት ድርድር እንደሌለ አሳውቀዋል። ይሁን እንጂ፣ መመሪያዎቹ ከነባራዊ ሁኔታው ጋር እንዲጣጣሙ ዳግም ለመመልከት ዝግጁ መሆናቸውን በመግለጽ ለውይይት በሩን ክፍት አድርገዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ውይይቱ በሁለቱ አካላት መካከል ያለውን ጥርጣሬና የጎሪጥ መተያየት በከፊል የቀነሰ ቢሆንም፣ አሁንም ድረስ “ጥራት” እና “ትርፍ” የሚሉት ሁለት ጽንፎች ሳይታረቁ ቀርተዋል።

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ወደ እውነተኛ የእውቀት ማዕከልነት ይሸጋገራል ወይስ በቁጥጥርና በቅሬታ አዙሪት ውስጥ እንደታሰረ ይቀጥላል? የሚለው ጥያቄ የብዙዎችን ትኩረት እንደሳበ ይገኛል።

ለዓለም አሰፋ



Source: Yeneta Tube

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2