የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ሐሙስ ዕለት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቴህራን ላይ ይፋ ያደረጉት “ኢኮኖሚ ጦርነት” ዘመቻ ዋሽንግተን ላይ “ተጨማሪ ሽንፈት” የሚያስከትል ነው አሉ።
አራግቺ በኤክስ ገጻቸው ላይ ” ‘የኢኮኖሚ ጦርነት’ የሚባለው ከአሜሪካ ቀውስ ትኩረትን ለማስቀየር” የተወሰደ እንደሆነ በመግለፅ የአገሪቱ ብሔራዊ ዕዳ 40 ትሪሊዮን ዶላር መድረሱን ከቀውሶቹ አንዱ አድርገው ጠቅሰዋል።
“ያልተሳኩ ፖሊሲዎችን አቅልሎ መመለከት የበለጠ ሽንፈትን እና የኢራናውያንን ጠላትነት ያመጣል” ያሉት አራግቺ፣ የአሜሪካ “ኢኮኖሚያዊ ሽብርተኝነት” በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ምጣኔ ሃብት እና ሉዓላዊነት አደጋ ላይ እንደሚጥል ተናግረዋል።
የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካዜም ጋሪባባዲ በኤክስ ገጻቸው ላይ ዋሽንግተን ወታደራዊ ዓላማዎቿን ማሳካት ባለመቻሏ ወደ “ኢኮኖሚ ጦርነት” ፊቷን አዙራለች ብለዋል።
“ኢራን ልትሸነፍ መቃረቧን፣ ከውድቀት አፋፍ ላይ መሆኗን ይናገራሉ፤ ነገር ግን አጋሮቻቸው እንዲረዷቸው እየተማጸኑ ነው” ሲሉ ጋሪባባዲ ተናግረዋል።
“ችግሩ የእነሱ የተሳሳተ ስሌት ነው። ለመሸፋፈን በሞከሩ ቁጥር፣ ለራሳቸው የበለጠ ውድቀት ይፈጥራሉ” ሲል አክለዋል።
“መከላከያው የጦርነቱን ዓላማዎች ማሳካት አልቻለም፤ እናም አሁን የሚቀጥለውን ውድቀታቸውን ‘ኢኮኖሚያዊ ጦርነት’ ብለው ሰየሙት።”
የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ይህንን ያሉት ትራምፕ ረቡዕ ዕለት “እስካሁን የትኛውም አገር ላይ ከተወሰደው የምጣኔ ሃብት ጫናዎች በበለጠ አድቃቂ የሆኑ የኢኮኖሚ እርምጃዎች” እንደሚወሰዱ ተናግረዋል።
ትራምፕ ይህንን ያሉት ለ60 ቀናት ተደርሶ የነበረው የተኩስ አቁም ስምምነት ሰኞ ዕለት ከተጠናቀቀ በኋላ ነው።
ትራምፕ ረቡዕ ምሽት ባጋሩት የማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፍ፣ ይህንን ኢኮኖሚያዊ እርምጃ የሚወስዱት የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ከአሜሪካ ጋር ስምምነት ላይ መድረስ ስላልቻለ መሆኑን ገልጸዋል።











No comments yet.