#Ethiopia | የኢትዮጵያ የሆርቲካልቸር ዘርፍ ከአበባ ኤክስፖርት ባሻገር በሙዝ፣ በአቮካዶ እና በሌሎች የፍራፍሬ ምርቶች የዓለም አቀፍ ገበያን በስፋት ለመቀላቀል የሚያስችለውን አዲስ የልማት ምዕራፍ መጀመሩ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ አትክልት፣ ፍራፍሬ እና አበባ አምራች ላኪዎች ማህበር (EHPEA) «ከሙዝ እሴት ወደ ላቀ ስኬት» በሚል መሪ ቃል ባዘጋጀው ሀገራዊ ጉባኤ ላይ ከ200 በላይ አምራቾች፣ የፖሊሲ አውጪዎች፣ የላቦራቶሪ ተመራማሪዎች እና የልማት አጋሮች ተሳታፊ ሆነዋል።
በጉባኤው ላይ የቀረቡት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የተባበሩት መንግስታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት (FAO) የዓለም የሙዝ ዓመታዊ ምርት 50 ሚሊዮን ቶን መድረሱንና ከዚህ ውስጥ እስከ 24 ሚሊዮን ቶን የሚሆነው በዓለም አቀፍ ንግድ እንደሚዘዋወር ያመላክታል።
ኢትዮጵያም ይህንን ሰፊ የገበያ ዕድል ለመጠቀም ባደረገችው ጥረት በተሻሻሉ የሙዝ ዝርያዎች የተሸፈነው መሬት 253,701 ሄክታር ማድረስ የቻለች ሲሆን ከ73 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ ተችሏል።
የማህበሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ እና የዘርፉ ተወካዮች እንደገለጹት ኢትዮጵያ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘውን የመካከለኛው ምስራቅ፣ የአውሮፓ እና የአፍሪካ ገበያዎችን በቀላሉ የመድረስ ሰፊ የተፈጥሮ እና ስትራቴጂካዊ ብልጫ አላት።
ሆኖም ይህንን አቅም ሙሉ በሙሉ ወደ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለመቀየር ከአግሮ-ሎጂስቲክስ፣ ከማቀዝቀዣ ኮንቴይነሮች ፣ ከፋይናንስ አቅርቦት እና ከቲሹ ካልቸር ላቦራቶሪዎች መስፋፋት ጋር የተያያዙ ችግሮችን በቅንጅት መፍታት እንደሚገባ ተመልክቷል።
መንግስት የነደፈውን የ10 ዓመት የሆርቲካልቸር ስትራቴጂ እና የብሄራዊ የፍራፍሬ ልማት እንቅስቃሴዎችን መነሻ በማድረግ ዘርፉን ወደ ቢሊዮን ዶላር ገቢ የሚያሸጋግሩ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በተለይም እንደ አቮካዶ እና እንጆሪ ያሉ ተፈላጊ ምርቶች የኤክስፖርት መጠን እያደገ የሚገኝ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአበባ ኤክስፖርት ያበጀውን የተቀላጠፈ የአየር ትራንስፖርት አሰራር ለፍራፍሬዎችም በምድር እና በባህር ትራንስፖርት በታገዘ የአግሮ-ሎጂስቲክስ ስርዓት በማገዝ ሀገሪቱን በአፍሪካ ቀዳሚ ተፎካካሪ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው።
በያፌት ገ/ህይወት
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu



Source: GetuTemesgen









No comments yet.