~ ቲክታከር “ጽጌ ሮያል”፤ ጽጌረዳ በቀለ
* ስፍራው የይቅርታና የቃል ኪዳን ምድር ነው፤ ይቅርታዋን ተቀብለናል!
~ የሃይማኖት አባቶቾ
#Ethiopia | በማህበራዊ ሚዲያ አውታሮች ላይ የቅዱስ ላሊበላን ገጽታና ታሪካዊ እሴት በሚያሳንስ መልኩ የተሰራጨው ትርክት ከፍተኛ ህዝባዊ ቁጣን ቀስቅሶ የነበረ ሲሆን ድርጊቱን የፈጸመችው በቲክቶክ “ጽጌ ሮያል” በመባል የምትታወቀው ጽጌረዳ በቀለ ወደ ስፍራው በአካል በመጓዝ ይቅርታ ጠይቃለች።
ግለሰቧ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከመንግስት አካላትና ከአካባቢው ተወካዮች ጋር በመወያየት ያደረገችው ድርጊት ስህተት መሆኑን አምናለች።
ወጣት ጽጌረዳ በቀለ የፈጸመችው ድርጊት አሳዛኝና ከባድ ጥፋት መሆኑን በመቀበል፣ ከህዝብና ከእምነቱ ተከተዮች ባሻገር ከፈጣሪ ጋር መጣላቷን በመረዳት ንስሐ እንደምትገባ ተናግራለች።
መላው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች እንዲሁም የቅዱስ ላሊበላ ተወላጆችና ወዳጆች ይቅርታ እንዲያደርጉላት በትህትና ጠይቃለች።
የቦታው የሃይማኖት አባቶች በበኩላቸው ስፍራው የይቅርታና የቃል ኪዳን ምድር መሆኑን በመጥቀስ፣ ጥፋቷን አምና በመምጣቷ ይቅርታዋን የተቀበሏት ሲሆን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚኖሩ የቅዱስ ላሊበላ ተወላጆችና ወዳጆችም ይቅርታዋን እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የቅዱስ ላሊበላ ደብር ጽህፈት ቤት፣ የቅዱስ ላሊበላ ደብረ ሮሃ ሰንበት ትምህርት ቤት እና የላሊበላ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ጽህፈት ቤት በጋራ ባወጡት መግለጫ፣ በከተሞች አካባቢ በዘፈን እየለመኑ “ላሊበላ” በሚል ስም የሚጠሩ አካላት ከዛጉዌ ሥርዎ መንግስት፣ ከቅዱስ ላሊበላ ታሪክም ሆነ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ምንም አይነት የባህልና የኑሮ ግንኙነት እንደሌላቸው አስታውቀዋል።
ቅዱስ ላሊበላ ንግሥናን ከክህነት፣ ክህነትን ደግሞ ከቅድስና ጋር አስተባብሮ ሀገር የመራ፣ አለም ያደነቃቸውን 10 ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ያነጸና ታላቅ ታሪካዊ አሻራ ያሳረፈ አባት እንጂ ከልመና ተግባር ጋር የሚገናኝ እንዳልሆነ አሳስበዋል።
የሃይማኖት አባቶችና የአካባቢው ተወላጆች ወደፊትም ቢሆን የቅዱስ ላሊበላን ትክክለኛ ታሪክ በትምህርት ካሪኩለምና በብዙኃን መገናኛዎች በትክክለኛው ይዘቱ የማስተዋወቅና የመሞገት ስራቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
ስለ ቅዱስ ላሊበላ ለማወቅ በአካል ቦታው ድረስ በመገኘት አባቶችን መጠየቅ እንደሚገባ የጠቆሙት አካላቱ፣ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የታሪክ ጥላሸት የሚቀቡ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡና መሰል ድርጊቶች ከተደገሙ ቅርሱን ለማስጠበቅ በህግ ደረጃ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስዱ አስታውቀዋል።
የላሊበላ ባህል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ጽህፈት ቤት
#Lalibela #LalibelaHistory #EthiopianOrthodox #EthiopianHistory #ZagweDynasty #LalibelaChurches #EthiopiaCulturalHeritage #ProtectEthiopianHistory #FaithAndForgiveness #RockHewnChurches #getutemesgen #getu #ጌጡ #ጌጡተመስገን #addisababa



Source: GetuTemesgen









No comments yet.