ኸርት ቱ ኸርት ቺልድረንስ ኤይድ በአንድ ዓመት ለአንድ ሺህ የልብ ሕሙማን ሕፃናት ነፃ ሕክምና የመስጠት መርሐግብር በጅማ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ለ 50 ሕፃናት ሕክምና በመስጠት በይፋ መጀመሩን አበሰረ።
ከጣልያን ሀገር የመጡ የሕክምና ባለሙያዎች ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሙያዎች ጋር በመቀናጀት የነፃ የልብ ቀዶ ሕክምና ለማከናወን ቅዳሜ ነሐሴ 23/2018 ዓ.ም ጠዋት ጅማ ከተማ ሲደርሱ የሆስፒታሉ ማህበረሰብ፣ አባገዳዎች፣ ሀደስንቄዎችን ጨምሮ የጅማ ከተማ ሕዝብ ደማቅ አቀባበል አድርገዋል። የሕክምና ቡድኑ ወዲያውኑ ወደሥራ በመግባት ሥራውን የጀመረ ሲኾን በቀጣይ ስምንት ቀናት ለ50 ሕፃናት ሕክምናውን እንደሚሰጥ አቶ ብርሃን ተድላ የኸርት ቱ ኸርት ቺልድረንስ ኤይድ መሥራችና የቦርድ ሰብሳቢ ገልፀዋል።
መርሐግብሩ በ 2019 ዓ.ም ዓመቱን ሙሉ በ10 የተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ከሚገኙ የመንግስት ሆስፒታሎች ጋር በመተባበር የሚቀጥል መሆኑን አቶ ብርሃን ጠቅሰው በአንድ ዓመት ጊዜ 1 ሺህ ሕፃናት ሕክምናውን ለማድረስ እንደሚሰራ አብስረዋል።
የመርሐግብሩ ዓላማ በተመለከተ ሲያብራሩም በትራንስፖርት ችግርና በአቅም ማነስ ምክንያት ሕክምና ማግኘች ያልቻሉ የልብ ሕሙማን ሕፃናት ባሉበት በመድረስ ሕክምናውን መስጠት እንዲሁም የሆስፒታሎችንና የዘርፉ ባለሙያዎች አቅም እንዲያድግ በማገዝ በቀጣይ ሥራውን ራሳቸውን ችለው እንዲያከናውኑ አመቺ ሁኔታ ለመፍጠር ታስቦ እየተከናወነ የሚገኝ መሆኑ ጠቁመዋል።
በመርሐግብሩ ላይ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚደንት ጨምሮ የሆስፒታሉ ከፍተኛ ሥራ መሪዎች ተገኝተው መልእክት አስተላልፈዋል።
በመርሐግብሩ ላይ የተገኙት አምባሳደር ፍፁም አረጋ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ባስተላለፉት መልዕክት የኸርት ቱ ኸርት ግብረሠናይ ድርጅት መሥራች አቶ ብርሃን ተድላ እና በሳቸው ግብዣ ከጣልያን ሀገር የመጡ የሕክምና ባለሙያዎች ለ1000 የልብ ሕሙማን ሕፃናት ነፃ ቀዶ ሕክምና ለመስጠት የታቀደውን ሰፊ መርሐግብር በዛሬው ዕለት በጅማ ሆስፒታል ለ50 ሕፃናት ሕክምና መስጠት የመጀመሪያውን መርሐግብር አስጀምረዋል። ይህን መርሐግብር አቅም ያላቸው ኢትዮጵያውያን ወገኖች፣ የዳያስፖራ ማኀበረሰብ አካላት በተጨማሪ እያንዳንዱ ዜጋ የማኪያቶ ወጪውን ጭምር በመለገስ ማገዝ እንዳለበት አሳስበዋል። ለዚህ ታላቅ መርሐግብር ስኬት ኢትዮጵያውያን የሕክምና ባለሙያዎች ጨምሮ ከጣልያን ሀገር የመጡ ባለሙያዎች እንዲሁም የጅማ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታልን አመራርና ባለሙያዎችን አመስግነዋል።



Source: FastMereja









No comments yet.