#Ethiopia | ኢትዮጵያ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርንና የሽብርተኝነት ፋይናንስን ለመግታት የምታደርገውን ጥረት ለማጠናከር የንግድ ድርጅቶች ትክክለኛ ባለቤቶቻቸውን ይፋ የሚያደርጉበትን ማዕከላዊ የመረጃ መዝገብ(Beneficial-Ownership Registry) በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ስር ልታቋቁም መሆኑንን ከብር ሜትሪክስ ሰምተናል።
ይህ አዲስ አሰራር በሀገሪቱ የፋይናንስና ንግድ ዘርፍ ላይ ጥብቅ ቁጥጥርን የሚጥል ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና የካፒታል ማርኬት ባለስልጣን ፈቃድ የሚሰጧቸውና የሚቆጣጠሯቸው ተቋማት የባለቤትነት መረጃቸውን አዘጋጅተው እንዲያቀርቡ የማስገደድ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።
በተጨማሪም በመንግሥት የግዥ ጨረታዎች ላይ የሚሳተፉ ኩባንያዎች የባለቤትነት መረጃቸውን ማሳወቅ የሚጠበቅባቸው ሲሆን በመረጃቸው ላይ የተገኘን ማንኛውንም ግድፈት በ5 የሥራ ቀናት ውስጥ ካላስተካከሉ ከመንግሥት ግዥ ጨረታዎች እስከ መታገድ የሚደርስ እርምጃ ይወሰድባቸዋል።
ብሔራዊ የሕገወጥ ገንዘብ ዝውውር መከላከል ኮሚቴ የመዝገቡን ምስረታ ለማፋጠን የሚያስችል የድርጊት መርሃ ግብር ያጸደቀ ሲሆን የመዝገቡን አሰራር የሚመሩ መመሪያዎች እስከ መስከረም 2019 ዓ.ም ይጸድቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቱን ገንብቶ ሙሉ በሙሉ እስከ መጋቢት 2019 ዓ.ም ተግባራዊ ለማድረግ አቅዷል።
ሆኖም አሁን ያሉት ኩባንያዎች መረጃቸውን ይፋ እንዲያደርጉ የተሰጣቸው የ6 ወራት ሕጋዊ ጊዜ የቴክኖሎጂ ስርዓቱ ሙሉ በሙሉ ከመዘረጋቱ አስቀድሞ የሚያበቃ በመሆኑ ሚኒስቴሩ ይህንን ሽግግር እስከ 2 ወራት ያህል ብቻ ሊያራዝመው ይችላል።
በሺዎች የሚቆጠሩ የግል ድርጅቶች የመጨረሻው የጊዜ ገደብ ከመጠናቀቁ በፊት እውነተኛ ባለቤቶቻቸውን በመለየትና በሰነድ በማደራጀት ለመመዝገብ ዝግጅት እንዲያደርጉ ታዟል።
በያፌት ገ/ህይወት
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu
Source: GetuTemesgen







No comments yet.