ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዓለም አቀፉ “Act For Early Years” ኢኒሼቲቭ የቅድመ ልጅነት እድገት ሻምፒዮን በመሆን እውቅና ተሰጣቸው
#FastMereja I የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዓለም አቀፉ “Act For Early Years” ኢኒሼቲቭ የ”ቅድመ ልጅነት እድገት ሻምፒዮን” በመሆን ከፍተኛ ዓለም አቀፍ እውቅና ተሰጣቸው። ይህ ታሪካዊ እውቅና የተሰጣቸው ከንቲባዋ እና የከተማ አስተዳደራቸው “የአዲስ አበባ የወደፊት ተስፋ የቅድመ ልጅነት እድገት ተነሳሽነት” በመቅረጽ ለሕፃናት አጠቃላይ እድገትና ደህንነት እያደረጉት ያለውን ሁለንተናዊ ኢንቨስትመንትና ቁርጠኛ አመራር በማስመልከት ነው።
ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው እውቅና የተበረከተው በየተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም አቀፍ ትምህርት ልዩ መልዕክተኛ እና የቀድሞው የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ጎርደን ብራውን በኩል የኢኒሼቲቭ አጋሮችን በመወከል ነው። ሂደቱም እንደ ዩኒሴፍ (UNICEF) እና ዩኔስኮ (UNESCO) ያሉ ታዋቂ ዓለም አቀፍ ተቋማት በተባበሩት የጋራ ጥረት አማካይነት እውን ሆኗል። “Act For Early Years” ኢኒሼቲቭ የሕፃናት የመጀመሪያዎቹ ዓመታት የእድገት ደረጃ በዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት አጀንዳዎች እና በመንግሥታት ዋና ዋና ፖሊሲዎች ማዕከል ላይ እንዲቀመጥ በትኩረት የሚሰራ ተቋም ነው።
ይህ የተሰጠው እውቅና አዲስ አበባን በአፍሪካ አህጉር ደረጃ የቀዳማይ ልጅነት እድገት ፕሮግራሞች የከተማ አመራር ተምሳሌትና ማዕከል ለማድረግ የሚደረገውን ዘርፈ-ብዙ ጥረት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያጠናክረውና ለሌሎች የአህጉሪቱ ከተሞችም አርአያ የሚሆን አዎንታዊ ተጽዕኖ እንደሚፈጥር ታምኖበታል።




Source: FastMereja








No comments yet.