የቅዱስ ላሊበላ የትርጓሜ ትምህርት ቤት ጉዞ

- Advertisement -
Sidebar AD


‎​ክፍል ፫

‎​#Ethiopia | በባለፈው ክፍላችን — በደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ የአዲስ ኪዳን ትርጓሜና ነገረ ድኅነት በህንፃዎቹ አሰራርና በመልከአ ምድራዊ አደረጃጀቱ እንዴት በቀጥታ ይገለጥ እንደነበር፣ የብሉይ እና የአዲስ ኪዳን ትስስር፣ እንዲሁም ከወቅቱ የግብፅ ጳጳስ ጋር ተያይዞ የተከሰተውን ታሪካዊ አጋጣሚ ተመልክተናል።

‎​በአሁኑ ክፍላችን ደግሞ የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ታሪክና የትርጓሜ ትምህርት ቤት በሂደት እንዴት ሊደክም እና ሊቋረጥ እንደቻለ፣ የታሪክ አጠናቃሪዎች ክፍተት ምን እንደነበረ፣ እንዲሁም ከዘመናት መቋረጥ በኋላ ትምህርት ቤቱ እንደገና እንዴት ሊያንሰራራ እንደቻለ የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ የአራቱ ጉባኤያት መጻሕፍት ትርጓሜ ትምህርት ቤት መምህር ሊቀ ሊቃውንት ሳሙኤል አስናቀ ከሰጡት ማብራሪያ ጋር አያይዘን እንመለከታለን።

‎​የታሪክ ድርሳናት እንደሚጠቁሙት በሀገራችን በነበሩ ፈታኝ የታሪክ አጋጣሚዎችና በተለይም በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ የሆነ የሥርዓትና የትምህርት መዋቅራዊ መደናቀፍ ገጥሟት ነበር።

‎ሊቀ ሊቃውንት ሳሙኤል አስናቀ እንደሚያስረዱት፤ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኋላ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከሃይማኖቱ መሠረታዊ እውቀትና ከነገረ መለኮት ምስጢር ጀምሮ የምታስተምረውን ያንን ጥልቅ ትምህርት ማስተማር አቁማ ቆይታለች። የቀደመው ታላቅ የጉባኤ ሥርዓት ደክሞ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ እንዳትዘጋና አገልግሎቱ እንዳይቋረጥ ብቻ በማሰብ የዜማና የጸሎት ሥርዓቱ ላይ ትኩረት ተደርጎ እንዲቀጥል የተደረገበት የታሪክ አጋጣሚ ነበረ።

‎​በደብረ ሮሃም ቢሆን በሂደት ከትርጓሜና ከሊቃውንት አንጻር የሚመጥን ተቋማዊ ትምህርት ቤት ሳይዘረጋ በመቆየቱ ምክንያት፣ ትምህርቱ እስከ መቋረጥ ደረጃ ደርሶ ነበረ። እንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት እንኳ ቀዳሽ ካህን አጥተው የተዘጉበት ጊዜ እንደነበረ ታሪክ ያሳያል። ኋላ ላይ በቦታው በነበሩ አስተዳዳሪዎች በተለይም እንደ አባ ብርሃነ ሥላሴ ባሉ አባቶች ጥረት በቦታው የተወለዱ ልጆች ሄደው የዜማውንና የድጓውን ትምህርት ተምረው እንዲመጡ በማድረግ ታላቅ እንክብካቤ ከተደረገ በኋላ አገልግሎቱ ሊቀጥል ችሏል።

‎​ይሁን እንጂ የታሪክ አጠናቃሪዎችና የጸሐፊያን ክፍተት ትምህርት ቤቱ በሂደት እንዲሸፈንና ታሪኩም እንዲደበዝዝ ካደረጉ ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱ ነበረ። ሊቀ ሊቃውንት ሳሙኤል አስናቀ እንደሚገልጹት፤ ቅዱስ ላሊበላ ለአገርና ለቤተ ክርስቲያን ያደረገው አስተዋጽኦ፣ በወቅቱ ሶሪያ ድረስ አራት ጳጳሳትን እስከ መሾም የደረሰበት ታላቅ መንፈሳዊ ተጽዕኖና በደብረ ሮሃ የነበረው ከፍተኛ እንቅስቃሴ በግልጽ ተጽፎ ወይም ተመዝግቦ ባለመያዙ ምክንያት እውነተኛው ታሪክ ሳይገለጥ ቆይቷል።

‎​በቅርብ ዘመናት ትምህርት ቤቱን እንደገና ለመተከል በተደረጉ ሙከራዎችም ቢሆን መሠረታዊ የታሰበ ተቋማዊ መዋቅርና እንክብካቤ ይጎድለው ነበረ። ሊቀ ሊቃውንት ሳሙኤል እንደሚናገሩት፤ ትምህርት ቤቱ ሲጀመር በጠቅላይ ቤተ ክህነት ደረጃ ለአንድ ተማሪ 70 ብር እየተከፈለ በጣም በጥቂት ተማሪዎች ነበረ የተጀመረው። ትምህርት ቤቱ ተቋማዊ ማህተም፣ ራሱን የቻለ ህግና የሂሳብ ደብተር፣ እንዲሁም የተደራጀ ጽሕፈት ቤት ሳይኖረው ለ24 ዓመታት ያህል በመቆየቱ ተማሪዎች በቂ ምግብና ማረፊያ አጥተው ይፈተኑ ነበረ።

‎​ተማሪዎች እዚያው ይገኙ በነበሩት መጋዘኖችና ተገቢ ባልሆኑ ቦታዎች እየተኙ፣ በታላቅ የመከራና የችግር ጉዞ ውስጥ አልፈዋል። መምህርና ደቀ መዛሙርቱ በዕለት ተዕለት ኑሮአቸው ስለሚበሉትና ስለሚያድሩበት ነገር እንዲጨነቁ መደረጉ ደግሞ ትምህርት ቤቱ በሚፈለገው ልክ ፍሬያማ እንዳይሆን አድርጎት ቆይቷል።

‎​በኋላም በ2015 ዓ.ም አካባቢ በመምህር ሊቀ ሊቃውንት ልብሰ ማርያም አራቱ ጉባኤ እንደገና እንዲከፈት ተደርጎ የነበረ ቢሆንም፣ በተከሰቱት የእንክብካቤና የትኩረት ማጣት ችግሮች ምክንያት ከስድስት ወራት ቆይታ በኋላ መምህሩ በመውጣታቸው ትምህርት ቤቱ እንደገና ተዘጋ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተበተኑ።

‎​ከዚህ ሁሉ ዘመናት መቋረጥና መደናቀፍ በኋላ ግን በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ በሊቃውንቱና በምዕመናን ጥረት ትምህርት ቤቱ እንደገና የሚያንሰራራበት አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ። በ2016 ዓ.ም ነሐሴ ፍልሰታ አካባቢ ወደ ቦታው የገቡት ሊቀ ሊቃውንት ሳሙኤል አስናቀ፣ በ2017 ዓ.ም መስከረም መጨረሻ አካባቢ ወንበር ዘርግተው የአራቱ ጉባኤያት መጻሕፍት ትርጓሜ ትምህርቱን በይፋ አስጀምረዋል።
‎​ሲጀምሩ የነበሩት የህንፃ፣ የስንቅ፣ የማረፊያና የመጻሕፍት እጥረት እጅግ ፈታኝ ነበሩ። ነገር ግን በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት መመሪያ፣ በአካባቢው ምዕመናንና ታላላቅ ገዳማት ድጋፍ ትምህርት ቤቱ እንደገና እንዲደራጅ ተደረገ። ለምሳሌ ከተከዜ ምዕራፈ ቅዱሳን አቡነ ሀዋሪያ ክርስቶስ ኪዳነምህረት አንድነት ገዳም ሁለት መነኮሳትን ለመማር ሲልክ የትምህርት ክፍሉንና ቤቱን ለመሥራት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን አምጥቶ ድጋፍ አድርጓል፤ ሌሎች አባቶችና ምዕመናንም እንዲሁ አብረው ቆመዋል።

‎​ዛሬ የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ የትርጓሜ ትምህርት ቤት ከ20 ወደ 60 በሚጠጉ ቋሚ ደቀ መዛሙርት አድጓል። ተማሪዎቹም ከተለያዩ ሀገራችን ክፍሎች ከትግራይ፣ ከኦሮሚያ፣ ከጉራጌ፣ ከጎንደር፣ ከሸዋና ከጎጃም የመጡ ናቸው። ትምህርት ቤቱም የቆየውን ባህላዊ አሰራር ከዘመናዊ አደረጃጀት ጋር በማጣመር የትምህርት፣ የስልጠና፣ የኮምፒውተር፣ የህዝብ ግንኙነትና የልማት ክፍሎችን አቋቁሟል።

‎​በተለይም ደቀ መዛሙርቱ ትርጓሜውን በቃል ከመያዝ ባለፈ በኮምፒውተር እንዲጽፉ፣ ጥናታዊ ጽሑፎችን በማዘጋጀት በጉባኤው ፊት አቅርበው እንዲተቹ፣ እንዲሁም ዘመናዊ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን (ላፕቶፖችና ፕሪንተሮችን) በመጠቀም እውቀታቸውን እንዲያዳብሩ ተደርጓል። ይህም ተማሪዎች የትምህርቱን ምስጢርና አረዳድ በጥበብ እንዲጨብጡ አስችሏቸዋል።

‎​የዚህ አዲስ ማንሰራራት ውጤት ደግሞ በበዓላት ወቅት መታየት ጀምሯል። ከተለያዩ ቋንቋዎች የመጡ ደቀ መዛሙርት የግዕዝንና የአማርኛን ትርጓሜ በሚገባ አጥንተው፣ በቅዱስ ላሊበላ በሚገኙ በ10 ቤተ መቅደሶችና በአካባቢው በሚገኙ ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት እንደ ገነተ ማርያም፣ ነአክቶ ለአብ፣ አሸተን ማርያም ና ይምርሃነ ክርስቶስና ባሉት ታላላቅ መድረኮች ወንጌልንና የሕማማት ትርጓሜን ፣ ውዳሴ ማርያም ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜን በብቃት መተርጎም ጀምረዋል። ይህ ስኬት ደብረ ሮሃ እንደ ቀደመ ታሪኳ የጥበብና የወንጌል ትርጓሜ ማዕከልነቷን እንደገና እየመለሰች መሆኗን የሚያበስር ህያው ምስክር ነው።

‎​በቀጣዩ ክፍል (ክፍል ፬ እና የመጨረሻው)፦

‎​የደብረ ሮሃ የትርጓሜ ትምህርት ቤት የወደፊት ራእይና የረጅም ጊዜ ግብ ምንድን ነው?

‎​ትምህርት ቤቱ ለአገራችንና ለዓለም አቀፉ መንፈሳዊ ማህበረሰብ የሚያበረክተው ዘላቂ አስተዋጽኦ፤





Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2