ኦርቢክስ ቴክኖሎጂስ የኢትዮጵያን ከተሞች የሚያዘምኑ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን ይፋ አደረገ

- Advertisement -
Sidebar AD


‎#Ethiopia | ​በኢትዮጵያ ከተሞች እየታየ ያለውን ፈጣን እድገትና የመሰረተ ልማት ስፋት ተከትሎ፣ የዜጎችን የእለት ተእለት ህይወት እና የአገልግሎት አሰጣጥን የሚያቀልሉ አዳዲስ የቴክኖሎጂ መፍትሄዎችን ይዞ መውጣቱን ኦርቢክስ ቴክኖሎጂስ አስታወቀ።

‎የኦርቢክስ ቴክኖሎጂስ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ስዩም ተስፋዬ እንደገለጹት፣ ድርጅታቸው እንደ ስታርትአፕ ካምፓኒ የዜጎችን እለታዊ እንግልት የሚቀንሱ እና ከተሞችን ዘመናዊ የሚያደርጉ አራት ዋና ዋና የቴክኖሎጂ አሰራሮችን አስተዋውቋል።

‎​እንደ አቶ ስዩም ማብራሪያ፣ የመጀመሪያው የቴክኖሎጂ መፍትሄ የመኪና ማቆሚያ ወይም የፓርኪንግ ችግርን የሚያቃልል ነው። በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች ዋና ዋና ከተሞች የተገነቡ የፓርኪንግ ቦታዎች ቢኖሩም፣ አሽከርካሪዎች በቅጽበት ትክክለኛውን መረጃ ለማግኘት እንደሚቸገሩ ጠቁመዋል።

ኦርቢክስ የሰራው ስርዓት ግን የግል እና የመንግስት የፓርኪንግ ቦታዎችን ወደ አንድ ማዕከላዊ የመረጃ ቋት በማምጣት አሽከርካሪዎች ባሉበት ሆነው ክፍት ቦታዎችን በስልካቸው እንዲያዩ፣ እንዲይዙ እና ያለምንም ሰው ንክኪ በራሳቸው አገልግሎት አግኝተው እንዲወጡ ያስችላቸዋል ብለዋል።

‎​ሌላው ሁለተኛው ስራ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የኃይል መሙያ ወይም የቻርጂንግ ስርዓትን ማዕከላዊ ማድረግ ሲሆን ኢትዮጵያ እስከ 2030 ድረስ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ወደ ስራ ለማስገባት እና በርካታ የኃይል መሙያ ጣቢያዎችን ለመገንባት ባስቀመጠችው እቅድ መሰረት፣ አገልግሎቱ በተበታተነ መልኩ እንዳይሰጥ “ኦርቢክስ ኢቪ “የተሰኘ የተቀናጀ መተግበሪያ አልምቷል።

‎አቶ ስዩም አክለውም፣ ይህ ስርዓት ተጠቃሚዎች በአንድ መተግበሪያ ብቻ የትኛውም ቦታ የሚገኝ የኃይል መሙያ ጣቢያን እንዲጠቀሙ ከማድረጉም በላይ፣ የአገሪቱን የኢነርጂ መረጃ ደህንነት በአገር ውስጥ የመረጃ ቋት ውስጥ ጠብቆ ለማቆየት እና የመንግስት አካላት የኃይል ፍጆታውን በአንድ ማዕከል እንዲከታተሉ የሚያስችል እንደሆነ ገልጸዋል።

‎​በሶስተኛ ደረጃ የቀረበው «አይ ሀብ» የተሰኘው የዜጎችና የመንግስት ግንኙነት ማጠናከሪያ መድረክ ሲሆን፣ ነዋሪዎች በመንገድ፣ በኤሌክትሪክ፣ በትራፊክ በድንገተኛ አደጋዎች ላይ የሚያዩአቸውን ችግሮች እና መረጃዎች በስልካቸው ለሚመለከተው የመንግስት አካል በቀጥታ እንዲያደርሱ ያደርጋል።

‎ስርዓቱ መረጃዎችን በየአካባቢው ክልል በመለየት እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት በመተንተን ለአስፈጻሚ አካላት የሚልክ በመሆኑ፣ ለቀረቡት ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እና በህዝብና በመንግስት መካከል ያለውን እምነት ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

‎«ኢትዮ ፓርክስ» የተሰኘው አራተኛው የቴክኖሎጂ ማዕቀፍ፣ በከተሞችና ከከተሞች ውጭ ያሉ የተፈጥሮ፣ የባህል እና የቪዲዮ መዝናኛ ቦታዎችን ዲጂታላይዝ በማድረግ ለአገር ውስጥ እና ለውጭ ሀገር ጎብኚዎች የሚያቀርብ ነው።

‎ተጠቃሚዎች የፓርኮችን መረጃ፣ የሚሰጡትን አገልግሎት እና የመግቢያ ክፍያዎችን አስቀድመው በመተግበሪያው በማጠናቀቅ የሚፈልጉትን መዝናኛ በቀላሉ ማግኘት ይችላሉ።

አቶ ስዩም ተስፋዬ ሲደመድሙ፣ ኦርቢክስ ተራ መተግበሪያ ሳይሆን አጠቃላይ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን የሚደግፍ እና ወደፊት ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ለማስፋፋት የታቀደ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ምህዳር መሆኑን አብራርተዋል።

‎ጌትነት ተመስገን
‎📷 ከበደ መክብብ

‎Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)

‎#getutemesgen #getu #ጌጡ
‎​#OrbixTechnologies ​#SmartCitiesEthiopia ​#DigitalEthiopia2025 ​#SmartMobility #SmartParking #UrbanMobility






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2