ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በኢትዮ-ኢስታንቡል ሆስፒታል በመገኘት የነፃ የልብ ቀዶ ጥገና ሕክምና ሂደትን ጎበኙ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ክቡር ታዬ አጽቀሥላሴ በኢትዮ-ኢስታንቡል ሆስፒታል ጉብኝት ማድረጋቸውን ተከትሎ በኢትዮጵያውያንና በውጭ ሀገር ስፔሻሊስቶች ትብብር የልብ ቀዶ ጥገና የተደረገላቸውን ሕፃናት አበረታተዋል።

ፕሬዝዳንቱ በቆይታቸው ሆስፒታሉ እያከናወነ ያለውን ዘመናዊ የሕክምና አገልግሎትና የበጎ አድራጎት ተግባር አድንቀው ዘርፉ ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገሩን ገልጸዋል።

ይህ የሕክምና አገልግሎት “Heart to Heart Children’s Aid” ፋውንዴሽን ባሰባሰበው ድጋፍና በኢትዮ-ኢስታንቡል ሆስፒታል ሙሉ ትብብር የተከናወነ ሲሆን በፕሮፌሰር ሳሻ የሚመራው የጣሊያኑ “ፔድሬ ፓዮ” የሕክምና ቡድንም በሥራው ላይ ተሳትፏል።

በዚህም በ12 ቀናት ውስጥ ብቻ በአዲስ አበባ 58 እንዲሁም በጅግጅጋ 16 በድምሩ የ74 ሕፃናት የልብ ቀዶ ጥገና በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል።

የሆስፒታሉ መስራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ብርሃን ተድላ እንደገለጹት ተቋሙ ባለፉት ሁለት ዓመታት ለ114 ሕፃናት 120 ሚሊዮን ብር የሚገመት የነፃ ሕክምና አገልግሎት ሰጥቷል።

ሆስፒታሉ በሦስት ዓመት ጉዞው ከ86 በላይ ሰብስፔሻሊስት ዶክተሮችን በመያዝ በልብ፣ በካንሰር፣ በደም ስርና በጭንቅላት ቀዶ ጥገና ዘርፎች ሰፊ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

አቶ ብርሃን አክለውም አገልግሎቱን ይበልጥ ለማስፋፋት ላቀረቡት የቦታ ጥያቄ መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በበኩላቸው በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ወደ ሀገራቸው ተመልሰው እንዲያገለግሉ ጥሪ አቅርበዋል።

እንዲህ ያሉ ተቋማት ዜጎች ለሕክምና ወደ ውጭ በመሄድ ከሚገጥማቸው እንግልትና ወጪ እንደሚታደጓቸውም ጠቁመዋል።

ፕሬዝዳንቱ በሕፃናቱና በቤተሰቦቻቸው ላይ የታየው ደስታ የተስፋ ብርሃን መሆኑን ገልጸው ለሕክምና ቡድኑ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በዕለቱ አስተያየታቸውን የሰጡ ወላጆች ልጆቻቸው ዳግም ሕይወት በማግኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል። ይህ የነፃ ሕክምና አገልግሎት በቀጣይ ወደ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይ፣ ሲዳማና ሌሎች ክልሎች ተደራሽ ለማድረግ ዕቅድ መያዙ ተጠቁሟል።

ለዚህ ስኬት አስተዋጽኦ ላደረጉት የጤና ሚኒስቴር፣ የጉምሩክ ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድና ሌሎች ተባባሪ አካላትም ከፍተኛ ምስጋና ቀርቧል።

#ኢትዮኢስታንቡልሆስፒታል #የልብሕክምና #በጎአድራጎት #ጤና #ታዬአጽቀሥላሴ #ኢትዮጵያ #getutemesgen #getu #ጌጡ #ጌጡተመስገን #addisababa






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2