#Ethiopia | በትውልድ ኢትዮጵያዊ የሆኑትና በእስራኤል የማካቢ አሽኬሎን እግር ኳስ ክለብ ባለቤትና የስፖርት አመራር አቶ ማንደፍሮ መኒ ያሶ በኢትዮጵያ ያደረጉትን የአንድ ሳምንት ጉብኝት በስኬት አጠናቀዋል።
ግለሰቡ በቆይታቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የስፖርት ትስስር ለማጠናከር የሚያስችል የሥራ ዕቅድ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በደብዳቤ አቅርበዋል።
አቶ ማንደፍሮ በቆይታቸው ወቅት ከተለያዩ የስፖርት ዘርፍ ኃላፊዎች ጋር ውጤታማ ውይይቶችን አድርገዋል።
ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ባህሩ ጥላሁን ጋር ባደረጉት ምክክር የእስራኤልን የእግር ኳስ ተሞክሮ ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት በተለይም በታዳጊዎች ሥልጠና ላይ በትብብር ለመሥራት ተስማምተዋል።
በተጨማሪም ከስፖርት ሚኒስትሩ ጋር በስፖርት ዲፕሎማሲ ዙሪያ የተወያዩ ሲሆን የተለያዩ የስፖርት አካዳሚዎችን በመጎብኘት የቁሳቁስና የሞራል ድጋፍ አበርክተዋል።
በአዲስ አበባ ስታዲየም በመገኘትም የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የሲዳማ ቡናን የሊግ ጨዋታ ተመልክተዋል።
ለሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ባቀረቡት የትብብር ጥሪ በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን አድንቀዋል።
ቀደም ሲል በሁለቱ ሀገራት የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች መካከል ለተፈረመው ስምምነት መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የነበራቸው አቶ ማንደፍሮ አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በእስራኤል የወዳጅነት ጨዋታ እንዲያደርግ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
በደብዳቤያቸውም ይህንን የስፖርትና የባህል ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በአካል ተገናኝተው ለመምከር ፍላጎት እንዳላቸው አስታውቀዋል።
አቶ ማንደፍሮ የጀመሯቸው የሥራ እንቅስቃሴዎች በሁለቱ ሀገራት የእግር ኳስ እድገት ላይ አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍቱ እየተነገረ ይገኛል።
#ኢትዮጵያ #እስራኤል #እግርኳስ #ስፖርት #ማንደፍሮመኒ #getutemesgen #getu #ጌጡ #ጌጡተመስገን #addisababa

Source: GetuTemesgen









No comments yet.