#Fastmereja: በኢትዮጵያ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓትን በማዘመን ረገድ ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተ የሚገኘው ቻፓ (Chapa) ፋይናንሻል ቴክኖሎጂስ፣ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ ለሰብአዊ ድጋፍና ለብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክቶች ላበረከተው ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ድጋፍ የክብር እውቅና ተሰጠው፡፡
“ከጋራ ስኬት ወደ ቀጣይ አገራዊ ተልዕኮዎች” በሚል መሪ ቃል በተሰናዳው የዕውቅና መርሃ ግብር ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሺፈራው ተሊላን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ቻፓ ከመንግሥት የቀረበለትን ጥሪ ተቀብሎ በሦስት ቀናት ውስጥ ብቻ ባበለጸገው “My GERD” የተሰኘ መድረክ፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከ230 ሺህ ዶላር በላይ ለህዳሴ ግድብ ድጋፍ እንዲያደርጉ ያስቻለ ሲሆን ኩባንያው ይህንን አገልግሎት ያከናወነው ያለ ምንም የኮሚሽን ክፍያ (Zero Commission) መሆኑ ተገልጿል።
በተመሳሳይ በ”አይዞን ኢትዮጵያ” (Eyezon Ethiopia) መድረክ አማካኝነት በ97 ሀገራት ከሚገኙ የዳያስፖራ አባላት ከ6.5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለሰብአዊ ድጋፍ የሚውል ገንዘብ እንዲሰበሰብ የቴክኖሎጂ መሰረት ሆኖ ማገልገሉ ተገልጿል።
ከብሔራዊ መታወቂያ (ፋይዳ) ጋር በተደረገ ስልታዊ ትስስር፣ እስካሁን ከ3.5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የመታወቂያ ክፍያቸውን በቻፓ በኩል በዲጂታል መንገድ ፈጽመዋል። ይህም ከ1.27 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመንግስት ገቢ እንዲሆን ማድረጉ በዝግጅቱ ላይ ተመላክቷል።
ቻፓ ከመንግስት ፕሮጀክቶች ባለፈ እንደ ከነማ ፋርማሲ ያሉ የግል ተቋማትን አሰራር እየቀየረ የሚገኝ ሲሆን የፋርማሲው ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሳሙኤል አበራ እንደገለጹት፣ ለ40 ዓመታት በጥሬ ገንዘብ ይሰራ የነበረው አሰራር በቻፓ አማካኝነት በ53 ቅርንጫፎች ወደ ዲጂታል ተቀይሯል።
በተጨማሪም ኩባንያው ከአዳማ ጀነራል፣ ከቅዱስ ጴጥሮስና ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታሎች ጋር የክፍያ ስርዓትን የማዘመን ስራ እየሰራ መሆኑ ነዉ የተገለፀዉ።
የቻፓ መስራችና ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ናይል ኃይለማርያም በበኩላቸው፣ “ቴክኖሎጂ ከገንዘብ ትርፍ ይልቅ ህዝብን ለሀገራዊ ዓላማ ለማስተሳሰር ሲውል የበለጠ ትርጉም ይኖረዋል” ብለዋል። ኩባንያው በቀጣይም “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030”ን ለማሳካት የሚደረገውን ጉዞ በቴክኖሎጂ ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ከተመሰረተ አጭር ጊዜ የሆነው ቻፓ በአሁኑ ወቅት ካሉት 40 በላይ ሰራተኞች መካከል 95 በመቶው ዕድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶች ሲሆኑ፣ 55 በመቶዎቹ ደግሞ ሴቶች መሆናቸው ተቋሙ ለስራ እድል ስብጥር የሚሰጠውን ትኩረት ያሳያል።



Source: FastMereja









No comments yet.