#Fastmereja: የትንባሆ ኢንዱስትሪ ወጣቶችንና ሕፃናትን በሱስ ለማጥመድ የሚጠቀምባቸውን አታላይ ስልቶች ለማጋለጥ ያለመ ዓለም አቀፍ ንቅናቄ በኢትዮጵያ በይፋ ተጀመረ፡፡
ዘመቻው በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ39ኛ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ34ኛ ጊዜ የሚከበረውን የዓለም የትንባሆ ነፃ ቀን ምክንያት በማድረግ የተጀመረ ሲሆን፣ “ለኒኮቲንና ለትንባሆ ሱስኝነት አጋላጭ የሆኑ ስልቶችን እናጋልጥ!” በሚል መሪ ቃል ዓመቱን ሙሉ በሚዘለቁ ተግባራት እንደሚታሰብ ተገልጿል።
በኢትዮጵያ የምግብና የመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን በመድሀኒት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ስዩም ወልዴ በሰጡት መግለጫ፣ የትንባሆ ኩባንያዎች እንደ ቸኮሌት፣ ቫኒላና ፍራፍሬ ያሉ ማራጭጣዕሞችን በመጠቀም አዲስ ትውልድን ኢላማ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።
አቶ ስዩም አክለዉም በተለይ የኤሌክትሮኒክ ሲጋራዎችን (Vape) እንደ ዘመናዊና ጉዳት እንደሌላቸው አድርገው በማቅረብ ወጣቶችን እያታለሉ እንደሚገኙና ጥናቶችም ኢ-ሲጋራ የሚጠቀሙ ወጣቶች ወደ መደበኛ ሲጋራ የመሸጋገር ዕድላቸው በ3 እጥፍ እንደሚጨምር አረጋግጠዋል ብለዋል።
ባለሥልጣኑ ባለፉት 9 ወራት ውስጥ ብቻ በ55,503 ተቋማት ላይ ጥብቅ ፍተሻ ማድረጉን የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ በዚህም ግምታዊ ዋጋቸው ከ9.7 ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ 1.3 ሚሊዮን ሕገወጥ ሲጋራዎችና 53 ኪሎ ግራም የትምባሆ ቅጠል እንዲወገዱ መደረጉን አስታውቀዋል።
በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሙሉእመቤት ታደሰ በበኩላቸው፣ በከተማ ደረጃ የሚደረገው ቁጥጥር ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልፀዉ እንደ GATS የጥናት መረጃ፣ ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ በኢትዮጵያ አጠቃላይ የትንባሆ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ5 በመቶ ወደ 4.6 በመቶ ዝቅ ማለቱ ትልቅ ስኬት መሆኑ ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ የትንባሆ ኢንዱስትሪውን የንግድ ፍላጎትና ጣልቃ ገብነት በመቋቋም ለሕዝብ ጤና ቅድሚያ በመስጠቷ የዘንድሮውን ዓለም አቀፍ እውቅና አግኝታለች።
የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) መረጃ እንደሚያሳየው በየዓመቱ ከ8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በትንባሆ ሳቢያ በሚመጡ እንደ ካንሰር፣ ልብ እና ስኳር ባሉ ሕመሞች ይሞታሉ፡፡
ከነዚህም ውስጥ 1.3 ሚሊዮን የሚሆኑት ራሳቸው ሳያጨሱ በሌሎች ጭስ ለህልፈት የሚዳረጉ ሲሆን ወላጆች፣ መምህራንና መገናኛ ብዙኃን የተቀናጀ ጥረት በማድረግ ወጣቶችን ከዚህ አደገኛ ወረርሽኝ እንዲታደጉ ባለሥልጣኑ ጥሪ አቅርቧል።
እንዲሁም በዛሬዉ እለት የአለም ከትምባሆ ጭስ ነፃ ቀንን ምክንያት በማድረግ የምክክር መድረክ የተካሄደ ሲሆን በዘርፉ ባለሙያዎች የተለያዩ ገለፃዎች የቀረቡ ሲሆን የፓናል ዉይይትም ተካሂዷል።



Source: FastMereja









No comments yet.