#Ethiopia | የአሜሪካ ፍትህ ሚኒስቴር ባለፈው የጆ ባይደን የፕሬዝዳንትነት ዘመን “በፖለቲካ ምክንያት ጥቃት ደርሶብናል” ለሚሉ የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎችና የቅርብ አጋሮች የሚከፈል የ1.776 ቢሊዮን ዶላር ፈንድ ማቋቋሙን አስታውቋል።
የአሜሪካን የነፃነት አዋጅ መታሰቢያ ዓመተ-ምህረትን በመውሰድ “የፀረ-መንግስት መሳሪያነት” የተሰኘው ይህ ፈንድ ይፋ ሊሆን የቻለው፣ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በግል ማንነታቸው በገቢዎች ባለስልጣን ላይ የመሰረቱትን የ10 ቢሊዮን ዶላር ክስ በፈቃደኝነት ማቋረጣቸውን ተከትሎ ነው።
በተደረገው ስምምነት መሰረት ለፕሬዝዳንት ትራምፕ ምንም አይነት ቀጥተኛ የገንዘብ ክፍያ የማይፈጸምላቸው ቢሆንም፣ የሀገሪቱ ፍትህ ሚኒስቴር ግን ለፕሬዝዳንቱ ይፋዊ የይቅርታ ደብዳቤ ያቀርባል።
የፍትህ ሚኒስቴር ጊዜያዊ ዋና አቃቤ ህግ እና የቀድሞው የትራምፕ የግል ጠበቃ ቶድ ብላንች በመግለጫቸው፤ የመንግስት መዋቅር በዜጎች ላይ እንደ ፖለቲካ መሳሪያ መሆን እንደሌለበትና ፈንዱ ቀደም ሲል የተፈጸሙ ስህተቶችን ለማረም የተዘረጋ ህጋዊ አሰራር መሆኑን አብራርተዋል።
ከታክስ ከፋዮች ህዝብ ገንዘብ የሚሸፈነውንና ይህንን ፈንድ የሚያስተዳድረውን ባለ አምስት አባላት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ትራምፕ የመሻርና የማባረር ሙሉ ስልጣን ያላቸው ሲሆን፣ የይገባኛል ጥያቄ ማቅረቢያው ጊዜ እስከ ታህሳስ 15 ቀን 2028 ዓ.ም ድረስ ክፍት ሆኖ ይቆያል።
ይህ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ እርምጃ ትራምፕ በገዛ እጃቸው በሚቆጣጠሩት የመንግስት ተቋም በኩል ለደጋፊዎቻቸው ክፍያ እንዲፈጽሙ የሚያስችል በመሆኑ፣ በዴሞክራቶችና በሙስና መከላከል ተሟጋቾች ዘንድ ከፍተኛ ትችትና ህጋዊ ክስ ሊገጥመው እንደሚችል ተነግሯል።
ትራምፕ ክሳቸውን ከመተውታቸው ጥቂት ደቂቃዎች በፊት 100 የሚሆኑ የኮንግረስ ዴሞክራቶች ለፍርድ ቤት ባስገቡት ሰነድ፤ ፕሬዝዳንቱ የግል ጥቅምን ማስከበር ላይ ያተኮረ ግልጽ አድሎአዊ አሰራር እየፈጸሙ ነው ሲሉ ከሰዋል።
ይህ አዲስ ስምምነት እንደ ማይክል ፍሊን እና ካርተር ፔጅ ያሉ የትራምፕ የቅርብ አጋሮች ከዚህ ቀደም ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር ካደረጓቸው የሚሊዮን ዶላር የካሳ ስምምነቶች ቀጥሎ የተመዘገበ ሌላኛው አነጋጋሪ ክስተት ሆኗል።
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu
#Trump #USA #JusticeDepartment #CompensationFund #USPolitics #Ethiopia
Source: GetuTemesgen









No comments yet.