#Fastmereja:- የጸረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች በጀርሞች መላመድን (AMR) ለመከላከል አስቸኳይና የተቀናጀ እርምጃ የማይወሰድ ከሆነ፣ እ.ኤ.አ በ2050 በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ወደ 10 ሚሊዮን ሊያሽቆለቁል እንደሚችል የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን አስታወቀ።
ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ይህንን ያስታወቀው፤ «የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድን ለመከላከል የተቀናጀ እርምጃ፡ የአንድ ጤናን በግንዛቤ እና በትምህርት ማሳደግ» በሚል መሪ ቃል፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ለ14ኛ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከበረውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ቀንን አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።
የጀርሞች መድኃኒት መላመድ (AMR) ማለት በሰውም ሆነ በእንስሳት ላይ ለሚከሰቱ ተላላፊ በሽታዎች ማከሚያ የምንወስዳቸው የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች (ለምሳሌ፦ አንቲባዮቲክስ፣ የቲቢ፣ የኤች.አይ.ቪ ወይም የወባ መድኃኒቶች) በሽታ አምጪ ጀርሞችን መግደል ወይም መቆጣጠር ሳይችሉ ሲቀሩ ሲሆን ጀርሞቹ መድኃኒቱን የመቋቋም አቅም ስለሚያገኟቸው በሰውነት ውስጥ ተከማችተው በመኖርና በመራባት ሕመሙ በቀላሉ እንዳይድን እንደሚያደርጉት አስታውቋል።
ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በሰጠው መግለጫ፤ ችግሩ በአሁኑ ወቅት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱንና በሰው፣ በእንስሳትና በአካባቢ ጤና እንዲሁም በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ቀውስ እያስከተለ እንደሚገኝ ጠቅሷል።
በአሁኑ ወቅት በየዓመቱ ከ750,000 በላይ ሰዎች በዚህ ምክንያት ህይወታቸውን እንደሚያጡና ወደፊት ሊደርስ የሚችለውን የሰው ህይወት መጥፋት ከመከላከል ባሻገር፣ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ሊደርስ የሚችለውን የ10 ትሪሊዮን ዶላር ከፍተኛ ኪሳራ (ከ2-3% የኢኮኖሚ ቅናሽ) ለመታደግ አስቸኳይ እርምጃ እንደሚያስፈልግ ግምቶች ማሳየታቸውን ባለሥልጣኑ ገልጿል።
በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በቂ የሕክምና ተቋማት፣ የንጹህ ውሃ አቅርቦት እጥረት ባለባቸውና ውስን ሀብት ባላቸው ታዳጊ አገራት ላይ የችግሩ አሳሳቢነት ይበልጥ ጎልቶ እንደሚታይም ተመልክቷል።
ይህንን ድምፅ አልባ ወረርሽኝ ለመከላከል ህብረተሰቡ መድኃኒቶችን በባለሙያ ትዕዛዝ ብቻ መውሰድና የግል ንጽህናውን መጠበቅ እንዳለበት ያሳሰበው ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ፤ ችግሩን መከላከል ለአንድ አካል ብቻ የሚተው ባለመሆኑ መላው ህብረተሰብ፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የጤና ባለሙያዎችና መገናኛ ብዙኃን በጋራ ሊረባረቡ እንደሚገባ ጥሪ አቅርቧል።
ዕለቱም በመጪው ሰኔ 8 ቀን 2018 ዓ.ም (June 15, 2026) በልዩ ልዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዝግጅቶች በአገር አቀፍ ደረጃ እንደሚከበር ታውቋል።
Source: FastMereja









No comments yet.