ኢትዮጵያ የአሜሪካን የ1 ቢሊዮን ዶላር የሰብዓዊ እርዳታ ከሚያገኙ ሀገራት ተርታ ተሰለፈች

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | ​አሜሪካ በተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (UNICEF) እና በዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) በኩል የሚተላለፍ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት ግዙፍ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊና የአደጋ ጊዜ እርዳታ እንደምትሰጥ አስታወቀች። ኢትዮጵያን ጨምሮ የዚህ የገንዘብ ድጋፍ ተጠቃሚ የሚሆኑ ከ40 በላይ ሀገራት የተለዩ ሲሆን እርዳታው በተለይም በግጭትበመፈናቀል እና በተፈጥሮ አደጋዎች ለተጎዱ ተጋላጭ ማኅበረሰቦች የሕይወት አድን አገልግሎት ለመስጠት ያለመ ነው።

​የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት እንዳስታወቀው ከጠቅላላው የገንዘብ መጠን ውስጥ ከ218 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለዩኒሴፍ እንዲሁም ከ800 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚሆነው ደግሞ ለዓለም የምግብ ፕሮግራም ይከፋፈላል። ይህ የገንዘብ ድጋፍ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሥነ-ምግብ እና የጤና አገልግሎቶችን ለማዳረስ እንዲሁም ንጹሕ የመጠጥ ውሃና የንፅህና አጠባበቅ ፕሮግራሞችን ለማስፋፋት ይውላል።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም ድጋፉን በደስታ የተቀበለው ሲሆን በዓለም ዙሪያ ለተከሰቱ የረሃብ ቀውሶችና ድንገተኛ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት አቅሙን እንደሚያጎለብትለት አረጋግጧል።

​በድርቅ፣ በግጭት እና በመፈናቀል ምክንያት ከፍተኛ የሰብዓዊ ድጋፍ ከሚሹ ሀገራት አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ ዩኒሴፍና የዓለም የምግብ ፕሮግራም የሚያደርጉትን የሕይወት አድን ሥራ በማጠናከር በኩል ከዚህ ዕርዳታ ትልቅ ተጠቃሚ ትሆናለች። ድርጅቶቹ በአሜሪካ መንግሥት እንደ “ታማኝና የተፈተኑ የሰብዓዊ አጋሮች” በመታየታቸው ይህን ሰፊ ኃላፊነት ሊወስዱ ችለዋል።

​ይህ ትልቅ የገንዘብ እርዳታ ይፋ የተደረገው በአሜሪካ የውጭ እርዳታ ፖሊሲ ላይ ሥር ነቀል ለውጥ ከተደረገ በኋላ መሆኑ ትኩረትን ስቧል። ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጥር 2025 (እ.ኤ.አ) ወደ ሥልጣን እንደተመለሱ፣ የአሜሪካን የውጭ ልማት እርዳታዎች ለ90 ቀናት በማገድ የዕርዳታ ፕሮግራሞችን ገምግመው የነበረ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ የዩኤስኤአይዲ (USAID) የኮንትራትና የድጎማ ስምምነቶችን ሰርዘው ነበር።

ይሁን እንጂ ዋሺንግተን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተመረጡ ዓለም አቀፍ ተቋማት በኩል የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቷን ቀስ በቀስ መጀመሯን ተከትሎ የተለቀቀው ይህ የ1 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ፣ የፖሊሲ ክለሳው ከተጀመረ ወዲህ በአሜሪካ ከተደረጉት የገንዘብ ድጋፎች በግዝፈቱ ቀዳሚው ሆኖ ተመዝግቧል።

Credit : The Reporter

በያፌት ገ/ህይወት

Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)

#getutemesgen #getu


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2