#Ethiopia | የሕፃናት መጻሕፍት ደራሲና የልጆች ፕሮግራም አዘጋጅ በመሆን፣ በተለይም “ቼሪ” የተሰኘውን ተወዳጅ የልጆች ገጸ-ባህሪ በመፍጠር በሕፃናት መዝናኛና ትምህርት ዘርፍ ጉልህ አሻራ ያሳረፈው ታዋቂው ኮሜዲያን አስረስ በቀለ፣ በድጋሚ የደግነት ተምሳሌትነቱን አሳይቷል።
ሰሞኑን በኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት (ወመዘክር) ካስመረቃቸው ሁለት አዳዲስ የሕፃናት መጻሕፍት መካከል የመጀመሪያውን መጽሐፍ ሽያጭ ገቢ ሙሉ ለሙሉ ለሙዳይ በጎ አድራጎት ድርጅት በስጦታ አበርክቷል።
ከ15 በላይ የልጆች ተረት መጻሕፍትን ለንባብ ያበቃው ደራሲ አስረስ በቀለ፣ ለሕፃናት ሥነ-ጽሑፍ ባበረከተው ከፍተኛ አስተዋፅኦ እ.ኤ.አ በ2022 በተካሄደው Ethiopia Reads Children’s Reading Summit ላይ እውቅና የተቸረው አንጋፋ ባለሙያ ነው።
ይህ የሰሞኑን ስጦታውም ጥበብን ከሕዝብ ወገንተኝነት ጋር አጣምሮ የመጓዙ ማረጋገጫ ሆኗል።
ይህንን ታላቅ የበጎ አድራጎት ስጦታ የተቀበለው የሙዳይ በጎ አድራጎት ድርጅት፣ ለረጅም ዓመታት በችግር ውስጥ ያሉ ሕፃናትን፣ እናቶችንና አረጋውያንን በመደገፍና ተስፋ በመሆን የሚታወቅ ተቋም ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በአቃቂ ቃሊቲ ወረዳ 2 አድራሻውን አድርጎ ሰብአዊ አገልግሎቱን በስፋት እየሰጠ ይገኛል።
የድርጅቱ መሥራች ወይዘሮ ሙዳይ ምትኩ የተደረገላቸውን ድጋፍ አስመልክተው ባስተላለፉት ልባዊ መልእክት፦
”አስረስ በቀለ (ቼሪ) የምንግዜም የልብ አጋራችንና ታማኝ ደጋፊያችን ነው። ዛሬም ይህንን የመጽሐፉን ገቢ ሙሉ ለሙሉ ለእኛ በማበርከት ያደረገልንን ታላቅ በጎ ተግባር ስንመለከት ከልብ የመነጨ ምስጋናችንን እናቀርባለን።”
በማለት አክለውም ለመላው የሀገራችንን ሕዝብ ጥሪ አቅርበዋል ”ሁሌም ከጎናችን የማትለዩ ደጋግ ኢትዮጵያውያን በሙሉ፤ ይህንን ጠቃሚ የሕፃናት መጽሐፍ በመግዛት፣ በአንድ በኩል የልጆቻችሁን የዕውቀት አድማስ እንድታሰፉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የሽያጩን ገቢ በቀጥታ ለሙዳይ በማዋል አቅመ-ደካሞችንና ሕፃናትን እንድትደግፉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።”
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu #ጌጡ


Source: GetuTemesgen









No comments yet.